የህይወት ቃል ህብረት Logo

በግምትና በነሲብ
የታጀበ አገልግሎት

ዕዝራ መጽሔት - ቁጥር ፪ - ታኅሣሥ ፪ሺህ ፪ (December 2009)

አንድ አገልጋይ አገልግሎቱን ባስታወቀበት ጽሑፍ “በፈውስና በተአምራት የታጀበ አገልግሎት ይሰጣል" ብሎ በድምቀት ጽፎአል። ሦስት ጊዜያት በአካል በመገኘት ሌሎች ሦስት ያህሉን በቪድዮ በመመልከት ብከታተለውም አገልግሎቱ በፈውስና በተአምራት ታጅቦ አላየሁትም። ይልቅስ ሌላ ሆኖ ነው ያገኘሁት።

ባደግኩባት ከተማ ውስጥ ዱሮ በጣም ጥቂት የእህል ወፍጮዎች ነበሩ። በአንዱ ወፍጮ ቤት የነበረው ሚዛን ተሰብሮ ከአገልግሎት ውጪ ሆኖ ነበር። ግን አቶ ዘውዴ የሚባል መዛኝ አለ፤ ዘውዴ የሚመጣው እህል በጆንያ ከሆነ በዓይኑ ገርምሞ፥ 50 ኪሎ፥ 70፥ 100 ኪሎ እያለ ክብደቱን ይናገራል። በዘንቢልና በከረጢት ከመጣ ደግሞ ብድግ አድርጎ እያስቀመጠ 12 ኪሎ፥ 8፥ 20 ኪሎ እያለ ማስፈጫውን ያስከፍላል። ዘውዴ የገመተውን መቀበል እንጂ “ልክ አይደለህም" ማለት አይቻልም። ሊል የደፈረ ሰው ከተገኘ ሴት ከሆነች ጥሬ እህሏን በዘንቢሏ፥ ወንዱም ዳውላውን ጥሬውን ተሸክሞ ወይም ጭኖ ወደ ቤቱ ይመለሳል ወይም ራቅ ወዳለው ወፍጮ ቤት ሊሄድ ይገደዳል። ገማቹ ዘውዴ ብዙውን ጊዜ እንደሚሳሳት የታወቀ ነው፡፡ ከአስሩ ምናልባት ሁለቱን ወይም ሦስቱን ትክክል ይሆናል። ሆኖም ማረጋገጫ የለም፤ ሚዛን የለማ! የነበረውም ወላልቆ እጥግ ተቀምጧል። ሚዛን ስለሌለ አስፈጪዎቹ የተባለውን ግምት ለመቀበል የውዴታ ግዴታ ሆኖባቸዋል። ግምቱ አልፎ አልፎ በአጋጣሚ ትክክል ሊሆን ይችላል። ከሆነ ትክክልነቱ በግምትና በነሲብ ብቻ ነው።

እኔ እሠራ ከነበርኩባቸው ቦታዎች በአንዱ እሠራ የነበረው የመሥሪያ ቤቱን ዕቃ ወደ ደንበኞች መላክ ነበር። ቅጹ ላይ ስሞላ የሚላከውን ዕቃ ክብደት በግምት ነው የምሞላው። የዕቃው ክብደት የሚሞላው ደግሞ በለመድኩት በኪሎ ሳይሆን በፓውንድ በመሆኑ ግምቴን ይበልጥ ከትክክል የራቀ ያደርገዋል። እኔ በግምት የጻፍኩትን አጓጓዥ ኩባንያው ይመዝነውና ትክክለኛውን ክብደት ጽፎ በማግስቱ የክፍያው ሰነድ ወደኔ ይመጣል። አንዳንዴ እስኪገርመኝ ድረስ እኔ የገመትኩት ክብደትና ትክክለኛው ክብደት መካከል የትየለሌ ርቀት መኖሩን አያለሁ።

በአገራችን በገጠሩም ሆነ በከተማው ማኅበረ ሰብ ዘንድ “አዋቂ" እየተባሉ አንድም የግምት አለያም አጋንንታዊ ከሆነ ምንጭ የሰዎችን ምስጢር የሚናገሩ ጠንቋይና አስማተኞች አሉ። እነዚህ ሰዎች የሚናገሩት በግምት ከሆነ ግምታቸው የተሰላና በብዙ ልምድ ያካበቱት መሳሳታቸው እንዳይታወቅ የሚከላከልላቸው ረቂቅ ግምት ነው።

በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ እንደ አቶ ዘውዴ የመሰለ ወይም እኔ ዕቃ ስልክ አደርግ እንደነበረው የመሰለ የግምትና የነሲብ ሥራ የሚሠሩ ወይም ጠንቋዮቹ የሚያደርጉትን የመሰለ ነገር የሚያደርጉ አገልጋዮች እልፍ ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ ይህን መሳይ የግምት አገልግሎት የሚታየው የ“መገለጥ" ስጦታ አለን በሚሉ ሰዎች ዘንድ ነው፡፡ ይህ ቃል በክርስቲያኑ ማኅበረ ሰብ ዘንድ የተለመደ ቃል ነው። ብዙ ክርስቲያኖች እንዲያውም የመገለጥ ስጦታ የሚባል ጸጋ እንዳለ በፍጹም ሳይጠራጠሩ ይቀበላሉ፡፡ ጸጋው ወይም ስጦታው ያላቸው ሰዎችም በሚቀጥለው ሳምንት ወይም ወር የሚሆነውን አስረግጠው የሚያውቁ፥ ሰዎች ያደረጉትንና ያሰቡትንም ሳይቀር እንደሚያውቁ ይመስላቸዋል። እንደዚህ ያሉ ሰዎች ወደሚያገለግሉበት ከሄዱ የተሰወረ ምስጢራቸው እንደሚራቆት ይፈራሉ።

ሌላው ይህ ስጦታ አለን የሚሉ ወይም አላቸው የሚባሉ የሚያደርጉት ነገር በጉባኤ ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉ በሽታና በሽተኞችን መጠቆምና መዳናቸውን ወይም መፈወሳቸውን መናገር ነው። በጉባኤው ብዙ በሽተኞችም ሊኖሩ ይችላሉ፤ ምንም በሽተኛም ላይኖር ይችላል። እነዚህን ነገሮች መጠራጠር ወይም 'ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አሠራርና አገልግሎት ነው ወይ?' ብሎ መጠየቅ ነውር ብቻ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ላይ እንደተቃጣ ወንጀልና እንደ ክህደትም ይቆጠራል፤ ይወገዛል፡፡ ኢመንፈሳዊነት ነው። ፈውስ ወይም ምልክት ወይም ተአምርና ትንግርት ተደረገ ከተባለ፥ 'አገልጋዩንም ምንጩንም ሳትጠረጥርና ሳትመረምር በደፈናው ተቀብለህ ብቻ መደነቅ አለብህ' የሚባል ይመስላል።ምልክቱና ፈውሱ አለመኖሩንም ልባችን እያወቀ ብቻ መገረምና መደመም አለብን። 'ለምን?' ሲባል 'ይህ በአእምሮ አይመረመርም፤ ልትደርስበት አትችልም፤ ስለዚህ ጭንቅላትህን ዝጋና የልብህን ትርታ ብቻ አድምጥ' ይባላል።

ለመሆኑ በቃሉ ውስጥ የመገለጥ ስጦታ ወይም የመገለጥ መደበኛ አገልግሎት ኖሮ ያውቃል? ወይም የዘመናችን የመገለጥ ስጦታ አለን ባዮች የሚያደርጉትን የመሰለ አሠራር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተደርጎ ያውቅ ነበር? እንዲህ የመሰለውን ስጦታስ እንደ ስጦታ እውቅናና ተገቢ መድረክ ሰጥተን ልንቀበለውና ልንገለገልበት ግዴታ ውስጥ መግባት አለብን? እንዳለብንና እንደሌለብን ከቀጣዮቹ ነጥቦች በመነሣት ወደ ድምዳሜ እንድንመጣ እፈልጋለሁ፡፡

1. በአዲስ ኪዳን ውስጥ...

በአዲስ ኪዳን ውስጥ የጸጋ ስጦታዎች በተዘረዘሩባቸው ክፍለ ምንባቦች ውስጥ ይህ 'የመገለጥ ስጦታ' የተባለ ነገር የለም። እነዚህ ዝርዝሮች በተጻፉባቸው በሮሜ. 12፤ 1ቆሮ. 12፤ ኤፌ. 5፤ እና 1ጴጥ. 5 ውስጥ ወደ ሃያ ያህል ስጦታዎች ሲጠቀሱ ይህ አለመጠቀሱ እንዲህ የሚባል ስጦታ ላለመኖሩ ተቀዳሚ ማስረጃ ነው።

2. ጌታም ሆነ...

ጌታም ሆነ በእግሩ ተተክተው ወንጌልን ተቀብለው ያስተላለፉልን የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት ይህን የመሰለ አገልግሎት አላገለገሉም። ይህን ስል አንድ የመገለጥ አገልግሎትን የሚመክት አገልጋይ ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህን የመሰለ ጸጋ ስለነበረው የሐናንያና ሰጲራን ጉድ በማውጣት መቅጣቱን ከሐዋ. 5 ጠቀሰ። በታሪክ ውስጥ የተጠቀሱ ክስተቶችን እንደ ትምህርትና አስተምህሮ አድርገን መውሰድ አይገባንም። የእግዚአብሔር መንፈስ በጨቅላዋ ቤተ ክርስቲያን ሊሆን ያለውን ነገር ለመከላከል አንድ ጊዜ ብቻ ይህን አደረገ እንጂ ደጋግሞ አላደረገም። ርስት ሽጦ ገንዘብ ከፍሎ ከማስቀመጥ የከፉ ነገሮች በአዲስ ኪዳን አልታዩም? እና ሁሉም ተቀሰፉ? ሌላው ነጥብ ጴጥሮስ ይህን የመቅሰፍት አገልግሎት ከዚህ አንድ ጊዜ ብቻ በቀር አላደረገም። ደግሞም ጴጥሮስ ሐናንያና ሰጲራን፥ “እዚህ ጉባኤ ውስጥ መሬትህን ሸጠህ ገንዘቡን የደበቅህ ሰው አለህ፤ እጅህን አሳየኝ. . " አላለም።

3. ይህ አሠራር...

ይህ አሠራር ብዙውን ጊዜ ወይ ከፈውስ ጋር አለዚያም ምስጢር ከመግለጥ ጋር ተቆራኝቶ ነው የሚታየው። እንደተገለጠ የሚታሰበው ወይም የሚገመተው “ምስጢር” ጉባኤውን ከቶውኑ እንዴት እንደሚያንጽና ከሆነም ምን ያህል እንደሚያንጽ ግልጽ አይደለም። ቀድሞውኑ እውነት መሆንና አለመሆኑ የሚጠራበት ማጥሪያም አይታይም። ከፈውስ ጋር የተቆራኘ ከሆነም መዘንጋት የሌለበት አንድ እውነት አለ። ያም ስሜታዊ ፈውስ (Psychosomatic healing) መኖሩ ነው። ይህ ማለት ዘላቂነት የሌለውና በሞቅታ ውስጥ የሚሰማ፥ በጊዜው ሰዎች ይሆናል ብለው የሚጠብቁትና የሚጓጉትን ነገር ሲነገር ከመናፈቅና ከመጠበቅ የተነሣ የሚለማመዱት፥ ይሆናል ተብሎ ስለተነገራቸውና የተባለውን ለመቀበልና ለማመን እንዲጠብቁ (Suggestibility Hyper-suggestibility ይሉታል) የሚፈጠር ጊዜያዊ ክስተት ነው። ስሜታዊ ሲባል ያለ የሚመስል ግን የሌለ ፈውስ እና የሌለ የሚመስል ግን ያለ ሕመም ማለት ነው። ይህ እንዴት እንደሚሆን አናውቅም ግን ይሆናል። ለምሳሌ፥ በጣም የምንጠብቀው እንግዳ ሲኖር በር የተንኳኳ ወይም የተደወለ ይመስለናል። እናቶች ሕፃን ከተኛ ተነስቶ ያለቀሰ የሚመስል ድምጽ ይሰማቸዋል። ስለዚህ ነው የተፈወሱ የመሰላቸው ሰዎች ወዲያው ወጥተው ይመሰክሩና በማግስቱና በሣልስቱ በሽታው በግርሻት የሚመለስባቸው። የ'ተአምራቱ' እና የ'ፈውሱ' አለመኖር ወይም የማይጨበጥ ሆኖ የኖረ መምሰል ስጦታው ላለመኖሩ ምስክር ሊሆን የሚችል ሁነኛ ዋቢ ነው፡፡

ይህ ማለት ታዲያ እውነተኛ የፈውስ ጸጋ መኖሩን እንዳንቀበል ማድረግ የለበትም። ፈውስና የፈውስ ስጦታ የለም ካልን ቃሉን መካዳችን ነው። የፈውስ ስጦታ በእርግጥ አለ። ቃሉ አለ ብሎ ከተናገረ ስጦታው አለ። ስጦታው ከኖረ የስጦታው ውጤትም አለ። የስብከት ስጦታ ከኖረ ስብከት እንደሚኖር ሁሉ የፈውስ ስጦታ ከኖረም ፈውስ አለ። በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ፈውሶች በተፈጸሙባቸው ቦታዎች ሁሉ ግብታዊ ነበሩ እንጂ ቀን ተመርጦላቸው፥ ቀጠሮ ተይዞላቸው፥ መርሐ ግብር ወጥቶላቸው፥ ታስበውና ተሰልተው አይደለም፡፡

ፈውስን በተመለከተ የመገለጥ ፈዋሾች ያሉትን ብቻ ሳይሆን የተፈወሱትም የሚሉትን እንዲሁም ፈውሱ በዘላቂነት መፈጸሙን መከታተል የዚህን የ'መገለጥ' አሠራር መኖርና አለመኖር ሊያመለክት ይችላል። ይህ አእምሮአዊ ፍለጋ የሥጋ ሥራ ተሰኝቶ ሊወገዝ አይገባውም። እርግጥ ነው መንፈሳዊ ነገር ከአእምሮ በላይ ነው፤ ይሁን እንጂ መንፈሳዊነት አእምሮን ማዳፈን አይደለም። ጌታ አእምሮአችንን ይከፍተዋል እንጂ አያዳፍነውም፤ መንፈስ ቅዱስም አእምሮአችንን ያድሰዋል እንጂ ያስወግደውም፡፡

ፈውስንና ምስጢር መግለጥን በግምትና በመላ የሚያደርጉ ሰዎች አንዳንዴ የሚሠራላቸው በአንድ መካከለኛ መጠን ያለው ጉባኤ ውስጥ በግምት የሚባሉት ነገሮች የመኖር እድል የሰፋ በመሆኑ ነው። 300 ሰዎች ባሉበት ጉባኤ ግራ ጎኑን የሚያመው ወይም ማኅጸንዋን የሚያማት፥ ወይም በሥጋዊ ባህርዩ ተሸንፎ አንድ ወይም ሌላ ኃጢአት የፈጸመ ሰው፥ ወይም አንድ ዕቃ አንድ ቦታ ያስቀመጠ ሰው እንደሚኖሩ የታወቀ ነው።

በተለይ ምስጢር አዋቂ መምሰልና ምልክት መስጠት ይህንንም የመገለጥ ስጦታ ብሎ እንደ አገልግሎት መቁጠርና ማስቆጠር የእግዚአብሔርን ሕዝብ ማገልገል ሳይሆን ማሰልሰል ነው፡፡ እግዚአብሔር በገዛ ሕዝቡ ውስጥ ምልክት የመናገር ግዴታ ውስጥ መግባት ለምን አስፈለገው? ሕዝቡ ስለማያምንና ወደ እምነት እንዲመጣ? ወይስ እግዚአብሔር ይበልጥ እንዲታመን? ደግሞስ ይህ የእግዚአብሔር ሁሉን አዋቂነት ምልክት ነው ወይስ የሰውየው መታወቂያ?

ጀርባችንን ለቃሉና ለታሪክ እንዲሁም እየሆኑ ላሉ ነገሮች መስጠት የለብንም። አይቶ እንዳላየ ለማለፍ በጆሮ ላይ ዳባ መለጠፍና አንገት ማጠፍ የግንባር ሥጋ ከመሆን ይጠብቀን ይሆናል። ነገር ግን ጉዳት አለው። ጉዳቱ ዘርፈ ብዙ ነው።

  • ሀ. አካል ይጎዳል። ተፈውሰሃል/ሻል ተብለው የማቀቁና የሞቱ ብዙ ናቸው። አካል ተጎድቶአል።
  • ለ. ስሜትም ይጎዳል። ካልተፈወሱ ያልተፈወስከው እምነትህ ጎድሎ ነው፤ ስላላመንህ ነው፤ አምነህ ስላልተቀበልክ ነው እየተባለ አካላዊው ጉስቁልና ሳይነሳ ስሜታዊ ቁስል ይጨመርባቸዋል።
  • ሐ. እምነታቸው ይጎዳል። ከእግዚአብሔር ጋር ጥለኞች ይሆናሉ፡፡ እግዚአብሔር ለእነርሱ የማይገደው፥ የማያስብ ይመስላቸዋል። ግንኙነታቸው ይበርዳል፤ ትጋታቸው ይቀንሳል።
  • መ. የሌሎችም እምነት ይናጋል። በተለይ አዳዲስ ክርስቲያኖች ግር ይላቸዋል፤ ግራ ይጋባሉ፤ በጥያቄ ይወጠራሉ። ገና አምነው ሳይጠግቡ ጥርጥር ይይዛቸዋል፡፡
  • ሠ. የቤተ ክርስቲያን ምስክርነት ይጎድፋል። ውሸታም ትሰኛለች፤ ቴያትር የምትሠራ ትመስላለች፤ (ቴያትር ደግሞ ቴያትር ነውና በቴያትር የሚሞቱ አይሞቱም) ለማያምኑ ቤተ ከርስቲያን የወንጌል መስሚያ በመሆን ፈንታ የድራማ መድረክ ትመስላለች፡፡
  • ረ. የጌታ ስም ይሰደባል። ይህ ከሁሉም የሚከፋው ነው። እነዚህ የግምት ሥራ የሚሠሩ አገልጋዮች የሚሠሩትን ሁሉ የሚሠሩት በጌታ ስም፥ “ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር" እያሉ በመሆኑ ሰሚዎች ጌታን ወክለው የሚናገሩ ይመስላቸዋል፡፡ ውጤቱ ተቃራኒ ሲሆን ግን ጌታ ተሰዳቢ ይሆናል። ይገርማል! በሽተኞቹም ጌታም ሲነቀፉና ሲሰደቡ የነሲብ አገልጋዮቹ ግን ከቶም አይነቀፉም። በዚህ ረገድ ብዙዎቹ ርቀው ሄደው ሃይ ከመባል አልፈዋል፤ ተፈርተዋል፤ የግምትና የነሲብ አገልግሎታቸው እንደ መደበኛ ጸጋ ተቆጥሮላቸው የቃልቻ ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛሉ። ጉዳቱ ቀላል አይደለም፤ ቁስሉ እንዳይሰፋ ግን ዝምታው ያብቃ፡፡