የኢሳይያስ ትንቢት ምዕራፍ 45፡1–5 በመላው ብሉይ ኪዳን ውስጥ እጅግ አስገራሚ፣ ጉልህና በምሁራን ዘንድ ሰፊ ክርክር የተደረገበት ሥነ-መለኮታዊ ክፍል ነው። ይህ ክፍል ለየት ያለ ትኩረት ሊያገኝ የቻለው፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) የአሕዛብ ንጉሥ የሆነውን የፋርሱን ታላቁን ቂሮስን "መሲሕ" ወይም "የተቀባ" በማለት በመሰየሙ ነው።ይህ ትንቢት ይፋ የሆነበት ታሪካዊ አውድ፣ የይሁዳ ማኅበረሰብ በባቢሎን ምርኮ ቀንበር ሥር ወድቆ፣ ብሔራዊና ሃይማኖታዊ ተስፋው ተሟጦ፣ በማንነት ቀውስ ውስጥ ይገኝ በነበረበት ወቅት ነው። በዚህ የውድቀትና የጨለማ ታሪክ ውስጥ፣ ነቢዩ ኢሳይያስ እግዚአብሔር በታሪክ መጋቢነት ላይ ያለውን ፍጹም የበላይነት የሚያውጅበትን ሥር ነቀል መልእክት ይዞ ብቅ ይላል። እግዚአብሔር የአሕዛብን ንጉሥ መርጦ "ቀኝ እጁን ይዤዋለሁ" (ኢሳ. 45:1) ማለቱ፣ የመለኮታዊ ሉዓላዊነት አድማስ ከእስራኤል ብሔራዊ ወሰን አልፎ፣ በዓለም መንግሥታትና በኃያላን ነገሥታት የፖለቲካ ሥልጣን ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለው የሚያሳይ እምቅ ምስክርነት ነው
ከክርስቶስ ልደት በፊት በ539 ዓ.ዓ የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ ታላቂቱን ባቢሎንን ድል ሲያደርግ፣ ይህ ክስተት በዓለማውያን ታሪክ ጸሐፊዎች ዘንድ እንደ ተራ ወታደራዊ ብልጫና የስትራቴጂ ውጤት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ነገር ግን፣ በቅዱሳት መጻሕፍት እይታ፣ ይህ ታሪካዊ ክስተት በመለኮታዊ መመሪያና ቀጥተኛ ጣልቃ-ገብነት የተከናወነ የታሪክ መለወጫ ምዕራፍ ነው።ጽሑፉ ቂሮስን "እረኛዬ" (ኢሳ. 44:28) እና "የተቀባው" ብሎ መጥራቱ ሁለት ዐበይት ሥነ-መለኮታዊ እውነታዎችን ያሳያል፦
የመለኮታዊ መሣሪያነት መርህ:- እግዚአብሔር ለገዛ ሕዝቡ መቤዠትና ነጻነት ሲል፣ ከቃል ኪዳኑ ማኅበረሰብ ውጭ ያሉትን ግዑዛን ኃይላትም ሆነ አረማውያን ነገሥታትን እንደ መሣሪያ ሊጠቀም ይችላል።
የሉዓላዊ ምርጫ ፓራዶክስ:- ቂሮስ እግዚአብሔርን በግል የማያውቀው አሕዛባዊ ንጉሥ ቢሆንም፣ ለእስራኤልና ለያዕቆብ ሲባል ልዩ መለኮታዊ ተልእኮ ተሰጥቶታል።ይህም በቁጥር 4 ላይ ባለው ኃይለ ቃል ይረጋገጣል፡-"ስለ ባሪያዬ ስለ ያዕቆብ፣ ስለ መረጥሁትም ስለ እስራኤል ስምህን ጠራሁህ፤ ባታውቀኝም በስምህ ጠራሁህ።"ይህ አገላለጽ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ታሪክ ለራሱ የድነት ዐላማ እንዴት በሉዓላዊነት እንደሚቀይስ የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው።
በቁጥር 5 ላይ የሚገኘው "እኔ እግዚአብሔር ነኝ፣ ከእኔም ሌላ ማንም የለም" የሚለው አዋጅ፣ በወቅቱ የነበሩትን ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ፍልስፍናዎች በቀጥታ የሚሞግት ሥነ-መለኮታዊ መግለጫ ነው። ይህ አዋጅ በተለይ በፋርስ ግዛት ውስጥ በስፋት ይንጸባረቅ የነበረውንና ዓለምን በሁለት ተቃራኒ ኃይሎች (በመልካሙ አሁራ ማዝዳ እና በክፉው አንግራ ማይንዩ) መካከል ያለ የዘላለም የትግል አውድ አድርጎ የሚመለከተውን የዞራስተርያኒዝም የሁለትዮሽ እምነት መሠረት ያናውጣል።ነቢዩ ኢሳይያስ እግዚአብሔር ብርሃንንም ሆነ ጨለማን፣ ሰላምንም ሆነ ክፉ ነገርን የሚፈጥር እርሱ ብቻ መሆኑን በቁጥር 7 ላይ በማወጅ፣ በዓለም ላይ መለኮታዊ ቁጥጥር የማይደረግበት ምንም ዓይነት ገለልተኛ ኃይል አለመኖሩን ያረጋግጣል።ይህ ዓይነቱ ፍጹም አንድነተ-መለኮት ምርኮኞቹ እስራኤላውያን በባቢሎን ሥልጣኔ ሥር ለጠፋው ብሔራዊና ሃይማኖታዊ ማንነታቸው ታላቅ ተስፋን ሰጥቷቸዋል። ያህዌ በባቢሎን ብሔራዊ አማልክት (በቤልና በናቦ) ላይ ሳይቀር ፍጹም የበላይ መሆኑን በማሳየት፣ ሕዝቡ በታሪክ ማዕበል ውስጥ ተስፋ እንዳይቆርጥ ተስፋዉን አድሷል።
የኢሳይያስ 45፡1–5 ትንቢት እግዚአብሔር በታሪክ ሂደት ውስጥ ያለውን ፍጹም እና የማይገሰስ ሉዓላዊነት በግልጽ ሲያሳይ፣ ቂሮስን የመሳሰሉ ዓለማውያን መሪዎችን ለቃል ኪዳኑ ሕዝብ መታደስና ለድነት ዕቅዱ ማስፈጸሚያነት መጠቀሙ፣ መለኮታዊው አሠራር በሰው ልጅ ሃይማኖታዊና ብሔራዊ ወሰኖች የማይገደብ መሆኑን ያረጋግጣል። የኮስሚክ ኃይላት የሁለትዮሽ ትግል የሚለው አመለካከት ፈጽሞ የተሳሳተ ነው። እግዚአብሔር የታሪክና የፍጥረት ብቸኛ ሉዓላዊ ጌታ ሲሆን፣ ይህ እውነት ለምርኮው ማኅበረሰብ የምሥራች እንደነበረው ሁሉ፣ ዛሬም የእግዚአብሔርን ዓለም አቀፋዊ መጋቢነት ለመረዳት እንደ ትልቅ የመሠረት ድንጋይ ለኛም ያገለግላል።
የኒዎ-አሦር ግዛት በ612 ዓ.ዓ በነነዌ ውድቀት መፈራረስ፣ በናቡከደነጾር ዳግማዊ ለሚመራው የኒዎ-ባቢሎን ግዛት ዓለም አቀፋዊ የበላይነት መንገድ ከፈተ። ይህ የኃይል ሚዛን መለወጥ በይሁዳ መንግሥት ላይ ጥቁር ጥላ አጠላ። በ597 ዓ.ዓ እና በ586 ዓ.ዓ የባቢሎን ኃይሎች ኢየሩሳሌምን በከባድ ከበባ ድል አደረጓት፤ የክብር ምልክት የሆነውን የሰሎሞንን ቤተ መቅደስም አወደሙት። በወቅቱ የነበረው ወታደራዊ ስልት የሀገሪቱን ምሁራን፣ ካህናትና የዳዊት ሥርወ-መንግሥት ወራሾችን በማፍለስ የሕዝቡን ማንነት መስበር ነበር። ይህ ክስተት መጽሐፍ ቅዱሳዊው ትንቢት "መቅደሴን አረከሱት... በእሳትም አቃጠሉት" (መዝ. 74:7) የሚለውን ሐዘን በተግባር ያሳየ ነበር።
"መቅደሴን አረከሱት... በእሳትም አቃጠሉት" (መዝ. 74:7)
ሥነ-መለኮታዊ ቀውስ፡ ያህዌ ወይስ ማርዱክ?
በ586 ዓ.ዓ. የባቢሎን ግዛት በንጉሥ ናቡከደነፆር መሪነት ኢየሩሳሌምን ሲያወድምና የእግዚአብሔር (ያህዌ) ማደሪያ ተብሎ የሚታመነውን የሰሎሞንን ቤተ መቅደስ ሲያቃጥል፣ ይህ ክስተት በይሁዳ ታሪክ ውስጥ ከፖለቲካዊና ወታደራዊ ሽንፈት እጅግ የላቀ ትርጉም ነበረው። በምርኮ ወደ ባቢሎን ለተወሰዱት እስራኤላውያን፣ ይህ ክስተት ብሔራዊ ውድቀት ብቻ ሳይሆን፣ የእምነታቸው መሠረት የተናወጠበት የጠለቀ ሥነ-መለኮታዊ እና የህልውና ቀውስ ነበር። "እግዚአብሔር ከተማውንና መቅደሱን ለምን አልጠበቀም? የተስፋው ቃል ኪዳንስ ፈረሰን?" የሚሉት ጥያቄዎች የማኅበረሰቡን ልቦና ክፉኛ ሞግተውታል።
የቃል ኪዳን ጥያቄ
ለአባቶች የተሰጠው "ዙፋኑ ለዘላለም ይጸናል" (2 ሳሙ. 7:16) የሚለው ተስፋ መክሸፉ፣ ሕዝቡን ለተስፋ መቁረጥ ዳርጓቸዋል።
የመገኘት ጥያቄ
ቤተ መቅደሱ ሲፈርስ፣ መለኮታዊው መገኘት ሕዝቡን ትቶ እንደሄደ ተሰማቸው።
ይህንን ሥነ-መለኮታዊ ቀውስ በሚገባ ለመረዳት፣ የጥንታዊውን መካከለኛው ምሥራቅ ዓለም አቀፋዊ የሃይማኖትና የፖለቲካ አስተሳሰብ ማጤን ግድ ይላል። በዚያን ዘመን በነበረው ሥነ-መለኮታዊ ዕይታ፣ በብሔራት መካከል የሚደረግ ማንኛውም ወታደራዊ ጦርነት በምድር ላይ ባሉ ሰብዓዊ ሠራዊቶች መካከል ብቻ የሚገደብ አልነበረም፤ ይልቁንም ብሔራቱን በሚወክሉት እና በሚጠብቁት ደጋፊ አማልክት መካከል በሰማያዊው ዓለም እንደሚደረግ የኮስሚክ ፍልሚያ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። በመሆኑም፣ የአንድ አገር ጦር መሸነፍ፣ የዚያ አገር አምላክ በአሸናፊው አገር አምላክ እንደተረታ፣ ኃይል እንዳጣና ግዛቱን ማስጠበቅ እንደተሳነው ተደርጎ ይተረጎማል።
ኢየሩሳሌም ስትወድቅ ባቢሎናውያን ይህንን ድል ወታደራዊ ብልጫቸው ብቻ ሳይሆን፣ የዋና አምላካቸው የማርዱክ ፍጹም የበላይነት ማረጋገጫ አድርገው ወስደውታል። በዚህ የሃይማኖት ፍልስፍናዊ አውድ ውስጥ፣ እስራኤላውያን ከባድ የስነ-ልቦና እና የእምነት ፈተና ላይ ወደቁ። "ያህዌ በባቢሎኑ ማርዱክ ተሸንፏልን?" የሚለው ልብ ሰባሪ ጥያቄ፣ በወቅቱ የነበረውን ከባድ የሥነ-መለኮት ችግር አጉልቶ ያሳያል። ያህዌ ከማርዱክ ያንሳልን? ወይስ ያህዌ ሕዝቡን ትቷል? እነዚህ ጥያቄዎች እስራኤላውያን ስለ አምላካቸው የነበራቸውን ብሔራዊና አጥቢያዊ ግንዛቤ ክፉኛ የሚፈትኑ ነበሩ።ይህንን አደገኛ ሥነ-መለኮታዊ ብዥታና የእምነት መፍረስ ለመታደግ፣ የብሉይ ኪዳን ነቢያት (በተለይም ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤል፣ እና የኢሳይያስ መጽሐፍ ሁለተኛ ክፍል) ራዲካል የሆነ የሃይማኖት ትርጓሜ ይዘው ብቅ አሉ። ነቢያቱ በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርተው እንዳስረገጡት፣ የኢየሩሳሌም ውድቀት የያህዌን የኃይል ድክመት ወይም በማርዱክ መሸነፍን የሚያሳይ አልነበረም። በተቃራኒው፣ ይህ ታሪካዊ ክስተት የያህዌን ፍጹም ሉዓላዊነትና የቅድስና ፍርድ በተጨባጭ የሚያሳይ ነው።
እስራኤላውያን የቃል ኪዳን ሕግጋቱን በመተላለፋቸው፣ በጣዖት አምልኮ በመርከሳቸውና ማኅበራዊ ፍትሕን በማጓደላቸው ምክንያት፣ ያህዌ ራሱ ባቢሎንንና ማርዱክን እንደ "የቁጣው በትር" በመጠቀም በገዛ ሕዝቡ ላይ የቅጣት ፍርድን አመጣ እንጂ፣ አቅም አጥቶ ወይም ተሸንፎ አልነበረም።በመጨረሻም፣ ይህ ጥልቅ ሥነ-መለኮታዊ ቀውስ ለእስራኤል እምነት ብስለትና መታደስ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። "ያህዌ ወይስ ማርዱክ?" ከሚለው አጣብቂኝ በመውጣት፣ ያህዌ የአንዲት አነስተኛ የይሁዳ ግዛት አምላክ ብቻ ሳይሆን፣ መላውን የዓለም ታሪክ፣ አሕዛብንና ታላላቅ ኢምፓየሮችን ጭምር በሉዓላዊነት የሚቆጣጠር፣ ታሪክን የሚዘውር ብቸኛ የዓለማት ጌታ መሆኑን ወደ ማመን አሸጋግሯቸዋል። ባቢሎንና አማልክቶቿ በእግዚአብሔር ዐላማ ውስጥ የተጫወቱት ጊዜያዊ የመሣሪያነት ሚና እንጂ፣ ከእርሱ ጋር የሚተካከሉ ተቀናቃኝ ኃይሎች አልነበሩም። ስለዚህ፣ ምርኮው የእስራኤልን እምነት ከማጥፋት ይልቅ፣ የእግዚአብሔርን ማንነትና አጽናፈ-ዓለማዊ ሉዓላዊነት ይበልጥ ጥልቅና ሰፊ በሆነ አውድ እንዲረዱት መንገድ የጠረገ ታሪካዊ መድረክ ሆኗል።
የ"ሁለተኛው ኢሳይያስ" ምላሽና አዲስ እይታ
በዚህ የጨለማ ወቅት፣ "ሁለተኛው ኢሳይያስ" (ኢሳ. 40–55) ቀውሱን የሚቀይር አዲስ ነገረ-መለኮታዊ አድማስ ይዞ መጣ። ነቢዩ ሁኔታውን የሚያቀርበው ያህዌ የተሸነፈ አምላክ ሳይሆን፣ ታሪክን የሚዘውር ሉዓላዊ ጌታ መሆኑን በማረጋገጥ ነው።
-
የመጽናናት ድምፅ፡ ስደቱ የአምላክ ድክመት ሳይሆን፣ ለሕዝቡ ቅድስና ሲባል የመጣ "የቁጣ ማስተካከያ" እንደሆነ ይገልጻል (ኢሳ. 40:1)።
-
ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት፡ ያህዌ የዓለም ፈጣሪና የነገሥታት ንጉስ ነው። "አሕዛብ በገንቦ እንዳለች ጠብታ ናቸው" (ኢሳ. 40:15) በማለት ባቢሎን በእግዚአብሔር ፊት ኢምንት መሆኗን ያውጃል።
-
የቂሮስ ሚና፡ እግዚአብሔር የባዕድ አገር ንጉሥ የሆነውን ቂሮስን እንኳ ለሕዝቡ ነፃነት መጠቀሙ፣ መለኮታዊ ሉዓላዊነት ከሃይማኖታዊ ድንበር በላይ መሆኑን ያሳያል።
የአካሜኒድ ፋርስ ግዛት እና የመለኮታዊ ጣልቃ ገብነት
የአካሜኒድ ፋርስ ግዛት መሥራች የሆነው ቂሮስ ዳግማዊ (በታሪክ 'ታላቁ ቂሮስ' በመባል የሚታወቀው) በ559 ዓ.ዓ ወደ ሥልጣን መምጣቱ፣ በጥንታዊው መካከለኛው ምሥራቅ ታሪክ ውስጥ የፖለቲካ፣ የባህልና የሥነ-መለኮት ዐዲስ ምዕራፍ የከፈተ አብዮታዊ ክስተት ነበር። ቂሮስ ሥልጣን በያዘ በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ የዘመኑን ታላላቅ ኃያላን መንግሥታት በተከታታይ በማንበርከክ የዓለምን የፖለቲካ ካርታ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል። በ550 ዓ.ዓ የሜዶንን ግዛት፣ በ546 ዓ.ዓ በሀብቷ የምትታወቀውን የልድያን ግዛት፣ እንዲሁም በ539 ዓ.ዓ የዓለምን ኃያል መንግሥትና የስልጣኔ ማዕከል የነበረችውን ታላቂቱን ባቢሎንን ያለ አንዳች ከባድ ደም መፋሰስ በቁጥጥሩ ሥር አዋለ። ይህ የኃይል ሚዛን ሽግግር፣ የዓለምን የበላይነት ከሴማዊ የሜሶጶጣሚያ ሥልጣኔዎች (ከአሦር እና ከባቢሎን) ወደ ኢንዶ-አሪያን የፋርስ ሥልጣኔ ያሸጋገረ ታሪካዊ ማዕበል ነበር።
የቂሮስ ፖሊሲና "የመቻቻል አዋጅ"
የቂሮስን "የመቻቻል ፖሊሲ" ታላቅነት ለመረዳት፣ ከእርሱ በፊት የነበሩት ኃያላን ግዛቶች (አሦራውያንና ባቢሎናውያን) ይከተሉት የነበረውን የጭቆና ስትራቴጂ ማጤን ያሻል። አሦራውያንም ሆኑ ባቢሎናውያን የተሸነፉ ሕዝቦችን ብሔራዊ ማንነትና የሥነ-ልቦና ጥንካሬ ለመስበር፣ በገፍ የማፈናቀልና በሌላ ባዕድ ባህል ውስጥ የማዋጥ ጭካኔ የተሞላበት ፖሊሲ ይከተሉ ነበር። ሕዝቦችን ከትውልድ ቀያቸው በመንቀል፣ መቅደሶቻቸውን በማፍረስ፣ እና አማልክቶቻቸውን (ጣዖቶቻቸውን) በመማረክ የብሔረሰቦችን ህልውናና የእምነት መሠረት ያጠፉ ነበር። የኢየሩሳሌም ውድቀትና የይሁዳ ሕዝብ ወደ ባቢሎን መማረክ የዚሁ ጨቋኝ ፖሊሲ ቀጥተኛ ሰለባነት ማሳያ ነው።
ታላቁ ቂሮስ ባቢሎንን ከተቆጣጠረ በኋላ ግን፣ ቀደም ሲል ከነበረው የአፈና ፖሊሲ ፍጹም በተቃራኒ የቆመ፣ በዘመኑ እጅግ አዲስና አብዮታዊ የሆነ የፖለቲካ ስትራቴጂ ተከተለ። ይህ ፖሊሲው "የመቻቻል አዋጅ" በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ በታሪክ "የቂሮስ ሲሊንደር" በሚባለው የሸክላ ላይ ጽሑፍ በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል። ይህ አዋጅ የሰዎችን ሃይማኖታዊና ባህላዊ መብቶች የሚያከብር በመሆኑ፣ በብዙ ምሁራን ዘንድ የዓለማችን የመጀመሪያው የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ ተደርጎ ይቆጠራል።
የእምነት ነፃነት
ሕዝቦች የራሳቸውን አማልክት እንዲያመልኩ ፈቀደ።
የተፈናቃዮች መመለስ
በምርኮ የነበሩ ሕዝቦች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አዘዘ።
የአምልኮ ተሃድሶ
የፈረሱ ቤተ መቅደሶች እንዲታደሱ ድጋፍ አደረገ።
በፖለቲካዊ መነጽር ሲታይ፣ የቂሮስ የመቻቻል አዋጅ ግዛቱን ሰላማዊ ለማድረግና የሕዝቦችን አመጽ ለማስቀረት የተቀየሰ ስትራቴጂ ሊመስል ይችላል። ሆኖም፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊውና ሥነ-መለኮታዊው ትርጓሜ ከዚህ የጠለቀ ነው። ለእስራኤላውያን፣ የቂሮስ አዋጅ (በዕዝራ 1 እና በ2ኛ ዜና 36 ላይ እንደተመዘገበው) የእግዚአብሔር ታማኝነትና የነቢያት ተስፋ ፍጻሜ ማረጋገጫ ነው።
አዋጁ እስራኤላውያን ከ70 ዓመታት የባቢሎን ምርኮ ነጻ ወጥተው፣ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱና የፈረሰውን የያህዌን ቤተ መቅደስ ዳግም እንዲገነቡ ታላቅ የታሪክ በረካ ሆኖላቸዋል። እግዚአብሔር የአሕዛብን ንጉሥ "እረኛዬ" እና "የተቀባው" በማለት ለገዛ ሕዝቡ መዳን ሲል እንደ ሉዓላዊ መሣሪያ አድርጎ መጠቀሙን፣ ይህ የቂሮስ የመቻቻል አዋጅ በተግባር አረጋግጧል።
የሥልጣን ሽግግር ሥነ-መለኮታዊ ትርጉም
የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ መነሳትና ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ የበላይነትን መቀዳጀት በኢሳይያስ 45 ላይ አስቀድሞ መጠቀሱ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሰው ልጅ ታሪክ ሂደት ውስጥ ያለውን ፍጹም እና የማይገሰስ የበላይነት ያሳያል። በአለማዊ የታሪክ ንባብ ፣ የንጉሠ ነገሥታት መቀያየር፣ የኢምፓየሮች መውደቅና መነሳት እንዲሁም የጂኦ-ፖለቲካዊ ኃይሎች መዋዠቅ እንደ አጋጣሚ ወይም እንደ ተፈጥሯዊ የፖለቲካ ዑደት ሊወሰድ ይችላል። ሆኖም፣ በመጽሐፍ ቅዱሳዊው የድነት ታሪክ አውድ፣ ይህ ክስተት ፈጽሞ አጋጣሚ አይደለም፤ ይልቁንም እግዚአብሔር ለሕዝቡ የገባውን የማይናወጥ የድነት ቃል ኪዳን ለመፈጸም የሚጠቀምበት ሉዓላዊ መሣሪያ ነው። ቂሮስ የያህዌን ህልውና በግል ባያውቀውም እንኳ፣ እግዚአብሔር "በስሙ የጠራው"፣ ገና ሳይወለድ ያሰበውና ለዚህ ታላቅ ዓላማ የሾመው መሆኑ፣ የመለኮትን የታሪክ መጋቢነት እጅግ አስደናቂ በሆነ መንገድ ያሳያል።
ይህንን ትንቢት ይበልጥ ለመረዳት የክፍሉን ሥነ-ጽሑፋዊ አውድ መመርመር እጅግ አስፈላጊ ነው። ኢሳይያስ 45፡1–5 ከምዕራፍ 40 እስከ 48 ባለው ሰፊ የትንቢት ክፍል ውስጥ ከፍተኛው የመልእክት ማዕከል ሆኖ ይገኛል። ምሁራን ይህንን የኢሳይያስ መጽሐፍ ክፍል "የመጽናናት መጽሐፍ" በማለት ይጠሩታል። እነዚህ ምዕራፎች የተነገሩት በባቢሎን ምርኮ ለነበሩት፣ የፖለቲካና የሃይማኖት ተቋማቶቻቸው (ቤተ መቅደሱና ዳዊታዊው ዙፋን) በመውደማቸው ምክንያት ብሔራዊ እና መንፈሳዊ ተስፋቸው ለተሟጠጠው፣ እንዲሁም በማንነት ቀውስ ውስጥ ለወደቁት እስራኤላውያን ነው። የእነዚህ ምዕራፎች ዋና ዓላማ የሕዝቡ የኃጢአት ቅጣት ማብቃቱንና የእግዚአብሔር የድነት ጊዜ መድረሱን ለማብሰር ነው።
የቂሮስ ትንቢት:
በዚህ የሥነ-ጽሑፍ መዋቅር ውስጥ ኢሳይያስ 45፡1–5 የትረካው ቁንጮ ነው። ነቢዩ የቂሮስን ማንነት የሚያስተዋውቅበት መንገድ ድንገተኛ ወይም ያልተቀነባበረ ሳይሆን፣ የራሱ የሆነ ኃይለኛ ጥበባዊ እና ሥነ-መለኮታዊ እድገት አለው። ክፍሉ የሚጀምረው "አጽናኑ፣ ሕዝቤን አጽናኑ፣ " (ኢሳ. 40፡1) በሚል አጠቃላይ የመለኮታዊ ጣልቃ ገብነትና የይቅርታ አዋጅ ነው።
ታሪኩ እያደገ ሲመጣ፣ እግዚአብሔር "ከምሥራቅ... ጻድቅን" (ኢሳ. 41፡2) እንዳስነሳ ይጠቁማል። በዚህ ጊዜ የአዳኙ ማንነት አልተገለጸም፤ ነገር ግን አንድ ኃያል ወታደራዊ ኃይል በባቢሎን ላይ እየመጣ መሆኑን ፍንጭ ይሰጣል።
ሥነ-ጽሑፋዊው ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ፣ ያልታወቀው አዳኝ ማንነት በመጨረሻ ይገለጣል፤ እርሱም "ቂሮስ" ተብሎ በስም ይጠራል። ከዚያም አልፎ "እረኛዬ" እና "መሲሑ" (የተቀባው) የሚሉ ከፍተኛ ሥነ-መለኮታዊ ማዕረጎች ይሰጡታል።
ይህ ደረጃ በደረጃ እያደገ የሚመጣው ሥነ-ጽሑፋዊ እርምጃ ፣ ምርኮኛውን ማኅበረሰብ ለማዘጋጀት እና ባልጠበቁት መንገድ፣ በአሕዛብ ንጉሥ በኩል፣ ነጻነታቸው በእግዚአብሔር እንደተረጋገጠ በጥበብ የቀረበ ትንቢት ነው።
- ኢሳይያስ 41:2–4፡ ድል አድራጊው "ከምሥራቅ" እንደሚነሳ በምስጢራዊ ሁኔታ ይገልጻል፣ ነገር ግን ስሙን አይጠቅስም።
- ኢሳይያስ 44:24–28፡ እዚህ ጋር ስሙ በግልጽ ይጠቀሳል። ያህዌ ቂሮስን "እረኛዬ ነው" ይለዋል። ኢየሩሳሌምም እንደምትታደስ ይናገራል።
- ኢሳይያስ 45:1–7፡ ይህ የመጨረሻው ደረጃ ነው፤ ያህዌ ቂሮስን "የተቀባ" ብሎ በቀጥታ ይጠራዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህ ማዕረግ የተሰጠው ብቸኛው አሕዛብ ንጉሥ እሱ ነው።
ዓላማው፦
የኢሳይያስ መጽሐፍ ምዕራፍ 45 በብሉይ ኪዳን ሥነ-መለኮት ታሪክ ውስጥ ፍጹም የሆነ የፓራዳይም ሽፍት ወይም የአስተሳሰብ ሥር ነቀል ለውጥ የታየበት ታላቅ ምዕራፍ ነው። ይህ ክፍል እግዚአብሔርን የእስራኤል "ብሔራዊ አምላክ" ብቻ ሳይሆን ፣ የዓለም ታሪክንና የፍጥረት ዓለምን ሙሉ በሙሉ የሚገዛ ፍጹም ሉዓላዊ ጌታ አድርጎ ይገልጸዋል።
በምርኮ ሥቃይና በማንነት ቀውስ ውስጥ ለነበረው የእስራኤል ማኅበረሰብ፣ ይህ ትንቢት እግዚአብሔር በታሪክ ጅረት ላይ ያለውን ፍጹም ሥልጣን የሚያረጋግጥበት መግለጫ ነው። እግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕዝቡን የታሪክ ዕድል ለመቀየር ምድራዊ ኃያላንን እንደ መሣሪያ የመጠቀም መለኮታዊ ነፃነቱንና ሥልጣኑን በሰፊው ይገልጣል።
በዚህ ምዕራፍ መጀመሪያ ላይ እጅግ አስገራሚና አነጋጋሪ ክስተት ይታያል፤ ይኸውም "መሲሕ" የሚለውን የተቀደሰና ከዳዊት ሥርወ-መንግሥት ጋር ብቻ የተያያዘውን ማዕረግ፣ አሕዛብ ለሆነውና ያህዌን ለማያውቀው ለፋርሱ ንጉሥ ለቂሮስ መስጠቱ ነው (ቁ. 1)። ኢሳይያስ 45:1 — "እግዚአብሔር ለቀባው ለቂሮስ... እንዲህ ይላል።"
ይህ አገላለጽ በወቅቱ ለነበሩት አይሁዳውያን እጅግ አስደንጋጭ ነበር። ምክንያቱም ቂሮስ የቃል ኪዳኑ አባል ያልሆነ፣ እግዚአብሔርን በግል የማያውቅና ሃይማኖታዊ ምልከታው የባዕድ የነበረ ንጉሥ ነው። ሆኖም ግን፣ በቁጥር 4-5 ላይ እንደተገለጸው፣ ቂሮስ እግዚአብሔርን ባያውቀውም እንኳ፣ እግዚአብሔር ግን ስሙን ጠርቶታል፣ ቀብቶታል፣ ለታላቅ ዓላማም አዘጋጅቶታል።
ይህ የሚያሳየው ሥነ-መለኮታዊ እውነት እግዚአብሔር ዓላማውን ለመፈጸም በቃል ኪዳኑ ሕዝብ ተቋማዊ አወቃቀር ወይም በዳዊት ሥርወ-መንግሥት ሰብአዊ መስመር ብቻ የተገደበ አለመሆኑን ነው። መለኮታዊው ፈቃድ ከሃይማኖታዊና ብሔራዊ ድንበሮች በላይ የመሻገር ፍጹም ነፃነት አለው። ቂሮስ እግዚአብሔርን ሳያውቅ መለኮታዊ ታሪክን የመሥራት አገልግሎት ውስጥ መሳተፉ፣ የእግዚአብሔር አሠራር ከሰብአዊ እውቀትና ፈቃድ በላይ መሆኑን ያስገነዝባል።
በቁጥር 5 ላይ የሚገኘው አዋጅ በብሉይ ኪዳን ታሪክ ውስጥ ካሉት የሞኖቴይዝም መግለጫዎች ሁሉ እጅግ ጠንካራውና የመጨረሻው ጥራዝ ነው፦ "እኔ እግዚአብሔር ነኝ፣ ከእኔም ሌላ ማንም የለም፤ ከእኔም በቀር አምላክ የለም።" ይህ አገላለጽ በሃይማኖት ታሪክ ውስጥ ትልቅ አብዮት የፈጠረ ነው። ቀደም ባሉት ዘመናት እስራኤላውያን ሌሎች የአሕዛብ አማልክት መኖራቸውን ሳይክዱ፣ ነገር ግን "ከሁሉ የሚበልጠውንና የእነርሱ የሆነውን ያህዌን" ብቻ የመምረጥና የማምለክ ዝንባሌ ነበረባቸው።
ነገር ግን በዚህ በምርኮ ዘመን ሥነ-መለኮት ውስጥ፣ የሌሎች ብሔራት አማልክት መኖራቸው የሌሉ መሆናችውን ያውጃል። የባዕድ አማልክት ህልውና የሌላቸው፣ የታሪክም ሆነ የፍጥረት ባዶዎች መሆናቸው ይታወጃል።
ይህ ጥብቅ የብቸኛ አምላክነት አስተምህሮ በወቅቱ በፋርስ ግዛት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ይስፋፋ የነበረውንና ዓለምን በመልካምና በክፉ ኃይሎች መካከል ያለ የዘላለም የትግል አውድ አድርጎ የሚመለከተውን የዞራስተርያኒዝም አስተሳሰብ በቀጥታ የሚሞግት ነው። በቁጥር 7 ላይ የሰፈረው ኃይለኛ ቃል ይህንን የሁለትዮሽ ፍልስፍና ይሰባብራል፦"ብርሃንን እሠራለሁ፥ ጨለማውንም እፈጥራለሁ፤ ሰላምን እሰጣለሁ፥ ክፉትንም (መከራን) እፈጥራለሁ፤ እነዚህን ሁሉ ያደረግሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ።"
እግዚአብሔር የብርሃንና የሰላም ብቻ ሳይሆን፣ የጨለማና የመከራም አዛዥና ፈጣሪ መሆኑን መግለጹ፣ በዓለም ላይ ከእግዚአብሔር ቁጥጥር ውጭ የሆነ ምንም ዓይነት ራሱን የቻለ የክፋት መለኮታዊ ኃይል አለመኖሩን ያረጋግጣል። ታሪካዊ ውድቀቶችም ሆኑ ስኬቶች፣ ምርኮም ሆነ ነፃነት፣ ሁሉም በአንድ መለኮታዊ ዕቅድ እና ሉዓላዊነት ሥር የሚንቀሳቀሱ ናቸው። ይህም በማንኛውም የፍጥረትና የታሪክ ክፍል ላይ የአንድ አምላክ ፍጹም ሉዓላዊነት የነገሠ መሆኑን ይደነግጋል።
ምዕራፉ የታሪክንና የፍጥረትን አንድነት በአጽንኦት ያሳያል። በቁጥር 8 ላይ ያለው ግጥማዊ መግለጫ እግዚአብሔር ታሪክን የሚዘውር ብቻ ሳይሆን፣ ተፈጥሮንም ለደኅንነት ዓላማ የሚያዝዝ መሆኑን ያሳያል፦"ሰማያት ሆይ፥ ከበላይ አንጠባጥቡ፥ ደመናትም ጽድቅን ያዝንቡ፤ ምድርም ትከፈት፥ ደኅንነትም ይብቀል..." እዚህ ላይ ፕሮቶሎጂ (የፍጥረት መጀመሪያ) እና ሶቴሪዮሎጂ (የደኅንነት ትምህርት) ተዋህደዋል። ሰማይና ምድር ለእስራኤል ቤዝዎት ሲባል ይንቀሳቀሳሉ። ተፈጥሮና ታሪክ በአንድ መለኮታዊ ቴሌዎሎጂ ውስጥ የተሳሰሩ ናቸው፤ እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሚሰጠውን ነፃነት ለመግለጥ መላውን ኮስሞስ ያንቀሳቅሰዋል።