የህይወት ቃል ህብረት Logo

እንስታዊ ስነ መለኮት

በዘላለም መንግሥቱ

ፒዲኤፍ ጽሁፉን ሙሉውን አውርድ

አንድ፤ መግቢያ

የእንስታዊነት ስነ መለኮት አቀንቃኞች ወይም አራማጆች የሆኑ እንስታዊ ስነ መለኮታውያን የዚህን ስነ መለኮት ጅማሬና ዳራ እጅግ ገፍተው መቶዎች ዓመታት ያስቆጠረ ሊያደርጉት ቢጥሩም ይህ ስነ መለኮት ከአርነት ስነ መለኮት ጋር እኩያ የሆነ የ1960ዎቹ ምርት ነው። ወደ ተሐድሶው ዓመታት የሚወስዱትም አሉ፡፡ ያ ግን ቀድሞ የነበረው የሮማዊ ክርስትና (ካቶሊካዊ) እንስታዊ አመለካከት ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተለየ ነውና ወደ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት መመለስን የጨበጠ፥ በሴቶቹ ሳይሆን በራሳቸው በወንዶቹ የተከወነ ትምህርት ነው፡፡ ከተሐድሶው በኋላ ሴቶች እንደ ቃሉ በሆኑ ተሳትፎዎች መሳተፋቸው ገሐድም አዳጊም እየሆነ መጣ።

1960ዎቹ ገዥዎች የጨበጧቸው ቅኝ አገሮች ነጻ የወጡባቸው፥ ኮሚኒስታዊ አመለካከት የተዛመተበት፥ በተለይ በአሜሪካ ደግሞ የሂፒ ንቅናቄ የተወለደበትና ያደገበት ዓመታት ናቸው፡፡ እነዚያ ዓመታት ብዙ ባህላዊ እሴቶች የተደፈጠጡባቸው፥ መንግሥታዊ፥ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ተቋማት የተናቁባቸው፥ ሥጋዊ አርነት፥ ግላዊ መብትና ኢተጠያቂነት የናኙባቸው ዓመታት ናቸው፡፡

እንስታዊነት ምንድር ነው? እንስታዊነት ርዕየተ ዓለማዊ (world view ወይም ideological) ንቅናቄ ሆኖ ሴቶች በማኅበራዊ፥ ባህላዊ፥ ምጣኔ ሀብታዊ፥ ፖለቲካዊ፥ ግላዊ፥ አካላዊ፥ ቀለማዊ፥ መደባዊ፥ ፆታዊ፥ (አሁን ከፆታዊ ጋር ፆታነታዊ ይጨመርበታል)፥ አእምሯዊ መድልዎ ወይም የበታችነት ይደርስብናልና፥ ከተባእት ፆታ ያነስን ሳንሆን በእኩልና በእኩልታ መታየት አለብን የሚል ንቅናቄ ነው።

እንስታዊነትን ካየን እንስታዊ ስነ መለኮትስ? እንስታዊ ስነ መለኮት ደግሞ እንደ እንስታዊ ንቅናቄ ሁሉ ሆኖ ስነ መለኮታዊ ገጽታ የያዘ፥ በሃይማኖቶች ውስጥ በሚደረጉ ሥራዎች፥ አገልግሎቶች፥ አመራሮች እኩላዊና እኩልታዊ (equality and equity) በሆነ መልኩ መሳተፍን ያነገበ ሃይማኖታዊ ንቅናቄ ነው። ይህ በሌሎች ሃይማኖቶችም በስሱ ተነስንሶ ቢገኝም በይሁዲነት በመጠኑና፥ በክርስትና ውስጥ በስፋት የሚገኝ የሚናዊ ነፃነት ጥያቄ ነው። ስነ መለኮታውያንም ይህንን ንቅናቄ ከቃሉ አንጻር መፈተሽ ሲጀምሩ፥ ጉዳይ ወይም ጥያቄ መሆን ብቻ ሳይሆን ንቅናቄም ሆኖ ወጣ።

የንቅናቄው መሪ አሳብ፥ መጽሐፍ ቅዱስ በልማዳዊው እይታ ሳይሆን በአዲስ ዓይን መታየት አለበት፤ መጽሐፍ ቅዱስ በሴትና በወንድ ያላደረገው ልዩነት በሰዎች የተደረገ ስነ መለኮትና አስተምህሮ ነውና መፈተሽ ብቻ ሳይሆን መስተካከል፥ አለፍ ሲልም መወገድ ያለበት ስሕተት ነው የሚል ነው። የእንስታዊ ስነ መለኮት መነሻና መንደርደሪያ ምንጮቹ መጽሐፍ ቅዱሳውያን አይደሉም። መጽሐፍ ቅዱስን ራሱንም ተጠየቅ ብለው ለምርመራ ሳይሆን በክስ የሚሞግቱ ናቸው፡፡

መነሻዎቹን ባህላዊ፥ አመለካከታዊ፥ እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ብለን ልንከፍላቸው እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሲባል የእግዚአብሔር በወንድ ፆታ መጠራት ሴትን ማጣጣል መምሰሉ፥ መልክና ምሳሌ አዳምን ብቻ ማስመሰሉ፥ ሴቶች ከወንድ እኩል አለመጉላታቸው፥ እና የመሳሰሉት ናቸው። ባህላዊ ችግሮች፥ የወንድ የበላይነት የሚንጸባረቅባቸው ባህሎች፥ የሴቶች ድርብ ጭቆናና ተያያዥ ጉዳዮች ሆነው፥ የአመለካከት ችግሮች ዘመን ወለድ ፍልስፍናዎችን የሚያነግቡ ናቸው፡፡

ሁለት፤ ፍጥረትና ውድቀት

እግዚአብሔር በፍጥረት ሥራው ሁሉን ፈጥሮ በስድስተኛው ቀን በመጨረሻ ሰውን ሲፈጥር በመልኩና በምሳሌው ነው የፈጠረው። "እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፡፡ እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።" ዘፍ. 1፥26-28።

በሦስቱም ጥቅሶች ውስጥ ግሶቹ የብዙ ናቸውና የእግዚአብሔር አምሳል አዳም ብቻ ሳይሆን ሔዋንም ናት። በዘፍ. 2፥7-8 እና 21-25 የአፈጣጠራቸው ዝርዝር ማብራሪያ ነው። አዳም ከአፈር መፈጠሩና ሔዋን ከአዳም ጎን ከተወሰደች አንዲት አጥንት መሠራቷ በምንም የተበላለጡ አላደረጋቸውም፡፡ አዳም ጥቂት ሰዓቶች ከሔዋን ከመቅደሙ በቀር ሁለቱም በአንድ ቀን የተፈጠሩ ናቸው፤ የሁለቱም ስምም አዳም ነበረ፤ ዘፍ. 5፥1-2 "የአዳም የትውልዱ መጽሐፍ ይህ ነው። እግዚአብሔር አዳምን በፈጠረ ቀን በእግዚአብሔር ምሳሌ አደረገው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፥ ባረካቸውም። ስማቸውንም በፈጠረበት ቀን አዳም ብሎ ጠራቸው።" አዳም ሁለቱም ናቸው፤ መልክና ምሳሌነት የአንዱ ብቻ አይደለም።

መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ሌሎች መጽሐፎችም በሚጻፉበት ጊዜ የወል ፆታ ስለማይጠቀሙና ከሁለቱ አንዱን ስለሚጠቀሙ ያ ፆታ ያንን አንዱን ብቻ የሚመለከት ነው ማለት አይቻልም። መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ በተጻፈባቸው 2 (3ኛም በትንሹ አለ) ቋንቋዎችም ይህ እውነት ነው። ከተሰጣቸው የጋራ ኃላፊነቶች ጥቅሶች እና "እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፡፡" ከሚለው በመነሣት፥ ሴት በፍጥረት መጀመሪያ የምትመች ረዳት እንጂ የበታች አለመሆኗን መረዳት ይቻላናል፡፡

የምትመች ረዳት ማለት አቻ አጋዥ እንጂ ምክትል ወይም የበታች ማለት አይደለም፡፡ የምትመች ረዳት እንጂ ተገዢ አልነበረችም። ቃሉ (ዔዜር) አጋዥ ወይም ረድኤት ማለት ነው። በሌሎች ጥቅሶችም፥ ለእግዚአብሔር ሰውን መርዳትም ጭምር ሲጠቀስ ምክትልነትንና የበታችነትን አያመለክትም። ለምሳሌ፥ ዘዳ. 33፥7፥ 26 እና 29፤ መዝ. 33፥20፤ 70፥5፤ ሆሴ. 13፥9፤ ወዘተ፡፡

ይህ ግንኙነት ለምን ያህል ጊዜ እንደቆየ ወይም፥ አዳምና ሔዋን ከተፈጠሩበት እስከወደቁበት ድረስ ምን ያህል ጊዜ በዔድን ገነት እንደቆዩ አናውቅም። ጥቂት ቀናት ወይም ጥቂት ሳምንታት፥ ጥቂት ወራት ወይም ጥቂት ዓመታት ቆይተው ይሆናል። አንድ ቀን ግን ኃጢአት ፈጸሙ። ኃጢአት ኖሮ ከእግዚአብሔር ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነትና ኅብረት ሊኖር አይቻልምና ተለዩ። ያ የመጀመሪያ ኃጢአት ጠቅላላውን የሰው ልጅ የጉዞ አቅጣጫ የቀየረና ሕይወቱንም ያበላሸ ክስተት ነበረ። ከተበላሹት ነገሮች አንዱ ግንኙነት ነው፡፡ ሰው ከራሱ ጋር፥ ሰው ከሰው ጋር፥ ሰእው ከእግዚአብሔር ጋር፥ ሰው ከፍጥረትና ስነ ምሕዳር ጋር ያላቸው ግንኙነት መልክ በዘላቂነት ተለወጠ፤ ታሪኩ በዘፍ. 3 ይገኛል፡፡

የአዳምና የሔዋን ግንኙነት ወይም ኅብረትም መልኩም ይዘቱም ተቀየረ። "ለሴቲቱም አለ፦ በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፥ እርሱም ገዥሽ ይሆናል።" ዘፍ. 3፥16። የሚስት ፈቃድ በባል ስር የሆነው በቀደመው የፍጥረት መርሐ ግብር ሳይሆን በኃጢአት በመውደቅ ምክንያት ነው። ከውድቀት በኋላ የፈቃዷ (ፍላጎቷ) ወደ ባሏ መሆንና እርሱ ገዥ መሆኑ ቀድማ የመሳቷ መዘዝ ነው፤ 2ቆሮ. 11፥3፤ 1ጢሞ. 2፥11-14።

ፍጥረት ላይ ትክክልና አቻ የነበሩት በውድቀት ግንኙነቱ መቅቀየሩ እውነት ነው፡፡

ሦስት፤ ወደቀ ማለት ተሰበረ አይደለም

የሰው በኃጢአት መውደቅ እውነት ቢሆንም፥ በሰው በኩል የመውደቅ ሂደቱ ለኳሽ ሔዋን ብትሆንም፥ ሰው ሁሉ በአዳም ቢወድቅም፥ ሴት በተለይ የተጣለች አልሆነችም፡፡ ያለፈውን ክፍል ስደመድም፥ ከውድቀት በኋላ የፈቃዷ (ፍላጎቷ) ወደ ባሏ መሆንና እርሱ ገዥ መሆኑ ቀድማ የመሳቷ መዘዝ ነው፤ (2ቆሮ. 11፥3፤ 1ጢሞ. 2፥11-14) በማለት ነበር። ኃጢአትን በተመለከተ ውድቀቱ ገሃድና ጠጣር ቢሆንም የተሰበረው ግንኙነት የመጠገን ተስፋ ተነገረ። መቅድመ ወንጌሉም ገና ከዔድን ሳይወጡ ተበሰረ። ወደቀ፥ ተሰበረ አልሆነም፡፡

በብሉይ ኪዳን ሕግ እና በአይሁድ ባህል የሴቶች ሚና መውለድና ማሳደግ ብቻ አይደለም። ይህ በራሱ ትልቅ ኃላፊነት እና በረከት መሆኑ መረሳት የለበትም። ሴት የምትመች ረዳትነቷ ወይም የወንድ አጋርነቷ ወይም አጋዝነቷ አልተሰረዘም። መጽሐፍ ቅዱስ፥ በተለይም ብሉይ ኪዳን የተጻፈበት ዳራ የሆነው የአይሁድ ማኅበረ ሰብ አባታዊ (patriarchal) ቢሆንም ሴቶችም ጉልህ ሥፍራ ነበራቸው። ቀጣዩን ትውልድ በመቅረጽ በኩል ሴቶች የተጫወቷቸው ሚናዎች ደማቆች ናቸው፡፡

የይስሐቅ ጭምትነትና ልስላሴ ምናልባት ከእናቱ የተወረሰ ሳይሆን አይቀርም። ሳራ በአብርሃም ውስጥ ጉልህ ስፍራ የነበራት ብቻ ሳይሆን በቀጣዩ ትውልድ የጉዞ ታሪክ የጣለችው አሻራም ነበረ። ርብቃ ወደ ይስሐቅ እንደምትሄድ ተጠይቃ ተስማምታ ነበር። ባትስማማ በግድ የምትሄድ አይመስልም፡፡ ለይስሐቅም ለዓመታት ለተቆጠረው ኀዘኑ የመጽናናት ምክንያትና ለልጃቸው ለያዕቆብ ደግሞ መካሪውና አቅጣጫ ጠቋሚው ነበረች። የሙሴ እናት ዮካብድ በሙሴ ልብ የከተበችው የታሪክ ክትባት እንደነበረ ባይጻፍም ይታያል። ሌሎችም ብዙ ሚስቶችና እናቶች የተጫወቷቸው አዎንታዊ የሴትነት ሚናዎች ተጽፈውልናል። የብሉይ ኪዳን ነገሥት ሲጠቀሱ፥ “እናቱም..." እየተባሉ የተጠቀሱ ሴቶች ብዙ ናቸው፡፡

መሪዎችም ነበሩ፡፡ ጎቶልያ ክፉና አስጨናቂ ንግሥት ሆና ነበር። ዲቦራ ሰፋኒት ሆና በእስራኤል ፈርዳለች። የእውነተኛ መሪነት ተግባር ሲመጣ ግን መሪነቱን ለባርቅ ነበር የለቀቀችው፡፡ በባዕድ አገር ንግሥት (ወይም የንጉሥ ሚስት) የሆነችው አስቴር ሕዝቧን በመሻቷ የታደገች ብልህና ደፋር ሴት ናት። በብሉይ ኪዳን ሴት ነቢያትም ነበሩ፤ ለምሳሌ ሕልዳና።

ወደ አዲስ ኪዳን ስንዘልቅ ጌታ ሴቶችን ዝቅ አድርጎ አልተመለከተም። ከአይሁድም ሴቶችን እጅግ ዝቅ አድርገው የሚያዩ ውሱን ልሂቃን ይኑሩ እንጂ ባህሉ እንደ ባህል፥ ሕዝቡ እንደ ሕዝብ ወይም ሕጉ እንደ ሕግ ሴቶችን አውጋዥ አይደለም፡፡ ሕጉ ሲጀመርም የእግዚአብሔር ቃል ነውና፥ የሕጉን ፈቺዎች አመለካከት እንጂ ሕጉን በምንም መልኩ መክሰስ አንችልም።

ጌታ ሴቶችን ዝቅ አድርጎ አልተመለከተም፤ የፈጠራቸው እርሱ ነውና ፍጥረታቸውን ያውቃል፡፡ ሲፈጥራቸው የሰጣቸውን ስፍራም ያውቃል። ከሴቶች ብዙ ደቀ መዛሙርት ነበሩ። ሆኖም አንዳቸውንም ከሐዋርያቱ መካከል አድርጎ አልጠራም። ምናልባት የአይሁድን ባህል ማጽደቁ የሚመስላቸው አሉ፡፡ ቢያደርግም ተቀባይ እንደማይሆኑም የሚገምቱ አሉ፡፡ እነዚህ ታዲያ ግምቶች ናቸው። ጌታ ከሐዋርያቱ ወይም ከመሪዎቹ መካከል ሴቶችን አለማድረጉ የቀደደው ፈር በቀጣዮቹ የቤተ ክርስቲያን ዘመናት የተከተሉትም ነው። ሐዋርያቱና የቀደመችው ቤተ ክርስቲያን አባቶች ጌታ ያላደረገውን አላደረጉም፤ ያደረገውንም አድርገዋል። ሴት ሐዋርያት እንዳልነበሩት፥ ሴት የቤተ ክርስቲያን መሪዎችም አልነበሩም። አንዳንድ አባቶችና ሊቃውንት ፈንገጥ ያለ አመለካከትና አቋም ቢኖራቸውም ያም የራሳቸው አቋም ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ በአጠቃላይ ሴቶችን አንኳሳሽ አይደለም፤ ሴቶችን አግናኝም አይደለም፡፡

አራት፤ ጸጋና ፆታ

ሴቶች የጸጋ ስጦታ የተነፈጋቸው የአካል ብልቶች አይደሉም፡፡ ለነገሩ፥ በአካል ውስጥ የሚገኝና የማያስፈልግ ምንም ብልት የለም። የጸጋ ስጦታ በፆታ ተለይቶ የተሰጠ አይደለም። ይህና ይህ የወንድ፥ ይህችና ይህች የሴት እየተባሉ የጸጋ ስጦታዎች አልተሰጡም፡፡

ሴቶች በወንዶች ላይ ሊሠለጥኑ ወይም በጉባኤ ሊናገሩ ወይም ሊያስተምሩ ያልተፈቀደባቸው ወይም ዝም እንዲሉ የተነገረባቸው ምንባባት (1ጢሞ. 2፥11-12፤ 1ቆሮ፣ 14፥34) ከጸጋ ስጦታ በፆታ ተለይቶ አለመታደል ወይም አለመነፈግ አሳብ ጋር የሚጋጩ ይመስላሉ። እንስታውያን ስነ መለኮታውያን እነዚህ ምንባባት ጥቂትና አጥቢያዊ ናቸው ብለው እንደሚያስተምሩት በአንዲት ትንሽ ከረጢት ውስጥ የምናስቀምጥበትና ዝቅ ዝቅ የምናደርግበት ምክንያት ባይኖረንም ለወንዶችና ለሴቶች ተለይቶ የተሰጠ የጸጋ ስጦታ አለመኖሩ ሴቶችንም አገልጋዮችም እንጂ ተገልጋዮች ብቻ እንደማያደርጋቸው ከአዲስ ኪዳን እናገኛለን። ጸጋንና ኃላፊነትን መለየትም ያስፈልገናል፡፡

እንዲህ ከሆነ፥ ማለትም የጸጋ ስጦታ በፆታ ተለይቶ ካልተሰጠ ሴቶች የማስተማርና ከመናገር ጋር የተያያዙ ስጦታዎች ሊኖሩአቸው ይችላሉ ማለት ነው። ከቻለ ታዲያ፥ ጥያቄው፥ እንዴት ይለማመዱታል? ወይም ይህን ጸጋ እንዴት ተግባራዊ ያደርጉታል? የሚለው ነው። አንድ መንገድ ላይ ኬላ ተደረገ ማለት ያ መንገድ ወደሚወስደው ስፍራ ሌላ ምንም መንገድ የለም ማለት አይደለም፡፡

ሴቶች ሴቶችን ሊያስተምሩ ይችላሉ፤ የሴቶችን አገልግሎቶች ወይም ቡድኖችን ሊያስተባብሩና ሊመሩ ይችላሉ፡፡ ቲቶ 2፥4-5 "ቆነጃጅትም የእግዚአብሔር ቃል እንዳይሰደብ፥ ባሎቻቸውን የሚወዱ፥ ልጆቻቸውን የሚወዱ፥ ራሳቸውን የሚገዙ፥ ንጹሖች፥ በቤት የሚሠሩ፥ በጎዎች፥ ለባሎቻቸው የሚታዘዙ እንዲሆኑ ይምከሩአቸው፡፡" ይላል። እነማን ናቸው፥ “ይምከሩአቸው' የተባሉት? የዐረፍተ ነገሩን ባለቤት ቁጥር 3 ላይ እናገኛለን። እንዲህ ይላል፤ "እንዲሁም አሮጊቶች ሴቶች አካሄዳቸው ለቅዱስ አገልግሎት የሚገባ፥ የማያሙ፥ ለብዙ ወይን ጠጅ የማይገዙ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚያስተምሩ ይሁኑ፤" ባለቤቱ አሮጊቶች ሴቶች ናቸው። ቃሉ ሽማግሌዎች የሚለው ቃል እንስታዊ አቻ ነው፡፡

በነዚህ ጥቅሶች ማስተማርም መምከርም ተጠቅሰዋል። የሚያያስተምሩ ሲል “ማስተማር ከተባለው የጸጋው ስጦታ ከተጠቀሰባቸው ቃል ጋር አንድ ነው፡፡ ይምከሩአቸው ሲልም አስተሳሰብን፥ አመለካከትን፥ ጤናማ፥ ጨዋና ጭምት ማድረግን፥ መቅረጽን የያዘ ቃል ነው። እነማን እነማንን እንደሚያስተምሩም በገሃድ ተቀምጦአል፤ አሮጊቶች ሴቶች ቆነጃጅቱን ወይም ወጣትና ጉብል የሆኑ ሴቶችን ነው። እንዲህ በመሰለው መቸት ሴቶች ልጆችንና ሴቶችን ሲያስተምሩ፥ ማንም ወንድ ለነዚህ የማኅበሩ ክፍሎች ሊናገር የማይችላቸውን ነገሮች እነርሱ ብቻ የሚናገሩት ብቻ ሳይሆኑ፥ ጥበባቸውና ተግባራዊ ትምህርታቸው ከተፈጥሮአዊ፥ ደመ ነፍሳዊ፥ ስሜታዊ ማንነታቸው፥ ከእውቀታቸውና በመንፈስ ቅዱስም ከተሰጣቸው ጸጋ ጋር ድንቅ ውጤትን ሊፈጥር እንደሚችል ፈጽሞም የማይጠረጠር ነው፡፡

አቂላና ጵርስቅላ አጵሎስን አስተምረውታል፤ ሐዋ. 18፥24-28። አጵሎስ ጉባኤ አይደለም፤ ግን ጉባኤን ማስተማር የሚችል የተጠቀጠቀ እውቀት ያለው አንድ ሰው ነው። የጢሞቴዎስ እናትና አያት ጢሞቴዎስን ከሕፃንነቱ ጀምሮ ቀርጸውታል፤ አስተምረውታል፤ 2ጢሞ. 1፥5 እና 3፥15። ጸጋው ካለ ሁሌም ጸጋውን የመልቀቂያ ክፍት በር አለ፡፡ ይሁን እንጂ ጌታ ከ12ቱ ሐዋርያቱ መካከል ሴቶችን ወይም መሪዎችን አለማድረጉ ብቻ ሳይሆን፥ ፋና ወጊ በሆነችው በመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያንና ቀጥሎ በተተከሉት አብያተ ክርስቲያናት ሴቶች የጉባኤ አስተማሪዎች ወይም መሪዎች ሲሆኑ አልታየም፡፡ ይህ፥ አንዳንድ እንስታውያን ስነ መለኮታውያን እንደሚሉት መጽሐፍ ቅዱስ ያላስተማረውና የኋለኞቹ አባቶች የፈጠሩት ትውፊት አይደለም።

ጌታ ከቀዳሚዎቹ ሴቶች ለምን ሐዋርያት አላደረገም? ባህሉን በማክበርና የሕዝቡን ስሜት ብቻ ተከትሎ ነው? ከሆነ ለጌታ ቅርብ ሆነው ያወቁትና የመጀመሪያዋን ቤተ ክርስቲያንና ቀዳሚዎቹን አብያተ ክርስቲያናት የመሩት ለምን አላደረጉም? ልብ እንበል ያ ዘመን የሮም ወግሪክ ባህል ዘመን ነው። ሴቶች ቀላል ያልሆነ ተሰሚነት እና ተጽዕኖ አሳዳሪነት አላቸው። ግን አላደረጉም። አንዳንድ ነገሮች መደረጋቸው ወይም አለመደረጋቸው እንጂ ለምን አለመደረጋቸው በዝርዝር አልተጻፈም። ይህ ማለት፥ “እነሱ ያደረጉት ወይም ያላደረጉት የተሰማቸውን ነውና እኛም የመሰለንን ማድረግ እንችላለን የሚል የፈቃድ ወረቀት አይሰጠንም። ወይም እነሱ ያላደረጉትን ነገር ከ2ሺህ ዓመታት በኋላ የተገኘነው እኛ እንድናደርግ የፈቃድ ወረቀት አይሰጠንም።

አምስት፤ ባህልና እንስታዊነት

ሴቶች የጸጋ ስጦታ የተነፈጋቸው የአካል ብልቶች አለመሆናቸውን አየን። የጸጋ ስጦታ በፆታ ተለይቶ አልተሰጠም ማለትና ግልጽ የሆነ የመሪነት፥ የአገዛዝ ወይም አስተዳደር ተግባርና ኃላፊነት በፆታ ተለይቶ አልተሰጠም ማለት የተለያዩ ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን እንደምናከብር ሁሉ ዝምታውንም እናከብራለን። የቤተ ክርስቲያን አባቶች ቃሉ ያላለውን፥ ያላዘዘውን አደረጉ ከተባሉ፥ ወይም ቃል ያዘዘውን ከለከሉ ከተባሉ በቃሉ ይዳኛሉ እንጂ ከእነሱ በተቃራኒ አቅጣጫ ተስፈንጥሮ መሄድ፥ '4+3=5 ነው።' ያለውን ሰው ለማስተካከል፥ 'የለም፤ 4+3=9 ነው።' እንደ ማለት ነው።

ክርስቲያን እንስታውያን፥ “ሴቶችን በጉባኤ ከመናገር፥ ከመምራት ወይም ከመሪነትና፥ ከማስተማርና ከመስበክ ያገዱት አባቶች ናቸው።‛ ካሉና ከተጻፈው አጉድለዋል ካሉ፥ እነሱ ደግሞ ያልተጻፈውን በተጻፈው ላይ መጨመር ወይም የተጻፈውን ጠምዝዘው የተመኙትን ማስባል አለባቸው ወይ? የለም፥ እነዚያ ምንባባት በባህል ዐውድ ነው መታየትና መፈታት ያለባቸው የሚለው ንግግር ብዙ የተባለ ነው። እርግጥም፥ ቃል በዐውዱ ነው የሚፈታው። ዋናው የቃሉ ዐውድ ራሱ ዙሪያ ገባው ቃሉ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ተጓዳኝ ከባቢዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ባህል ከነዚህ አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡

የትኛውም ማኅበረ ሰብ ልማድ፥ ባህልና ወግ አለው። እነዚህ ነገሮች የሌሉት ማኅበረ ሰብ የለም። በየባህሉም የማኅበረ ሰቡ የተለያዩ ክፍሎች ውሱን ሚና አላቸው። ወንዶች፥ ሴቶች፥ ወጣቶች፥ ጎልማሶች፥ አረጋውያን፥ ወዘተ፥ ዕድሜያዊ ወይም ፆታዊ ሚና አላቸው። አንዳንዶቹ ታሳቢና ተጠባቂ ሲሆኑ ሌሎቹ ግልጽ ናቸው። የክርስትና ወይም የቤተ ክርስቲያን ዋና ዳራ በሆነው የአይሁድ ባህልም ሆነ ክርስትና በተወለደበት የሮም ወግሪክ ባህል የሴቶች ሚና ይታወቃል፡፡ በጥቅሉ ሲታይ፥ ከመስክ ይልቅ የቤት፥ ከአደባባይ ይልቅ የማጀት፥ ከውጪያዊ ይልቅ ውስጣዊ፥ ከመጉላት ይልቅ ጭምትነት፥ ከፊታውራሪነት ይልቅ የደጀንነት ተግባር ነው። ይህ ሁሌና በሁሉም ባይባል እንኳ በሁሉም ማለት እስኪቻል ድረስ ያለው ባህላዊ የፆታ ሚና ነው፡፡

ክርስትና የአይሁድ ባህል ፎቶ ኮፒ አይደለም። ወንጌል በባህሎች ውስጥ ሲሰበክ ባህልን ሳይሆን ሰዎችን ነው የሚለውጣው። ሰዎችንም ከውስጥ ወደ ውጪና ወደ አካባቢ የመለወጥ ሂደት ነው፡፡ ባህል ከተለወጠ የዚህ የሰው ውስጣዊ ለውም ውጤት ነው። (ስለዚህ ጉዳይ በመጠነኛ ስፋት የጻፍኩትን የባህል ስነ መለኮትን ተመልከቱ፡፡)

በባህል ውስጥ ያለና በቃሉ ውስጥ የሌለ መልካም እሴት የለም። በባህል ውስጥ የሌለና በቃሉ ውስጥ የሚገኝ መልካምነት ግን ሁሌም አለ። ለምሳሌ ሁሉም ባህል አትበቀል አይልም። የሚል አይጠፋ ይሆናል፤ ብዙዎች ግን እንዲያውም ያበረታቱታል፡፡ ወንጌል ወደ ሰዎች ባህል ሲመጣ ጎጂዎቹ ይቀራሉ ወይ ይቀየራሉ። ይሁን እንጂ የወንጌል ግብ ባህል ቅየራ አይደለም፡፡

እንስታዊ ሚና ከባህል ባህል ይለያያልና የወንጌል ወደዚያ ባህል መድረስ የባህል አብዮት ማካሄድ መሆን የለበትም። በሂደት የሚለወጡ ጎጂ ባህሎችን ከውስጥ ወደ ውጪ መለወጥ ከሆነ እንስታዊ ሚናም ከቃሉ ጋር በተያያዘ መልኩ መታየት አለበት፡፡ መሪነትን በተመለከተ፥ ሴቶች ብቻ በሚገኙበት ጉባኤ ወንዶች እስኪኖሩ መሪ አይኖርም ማለት ነው? አይደለም። ወንድ ኖሮም ያ ሰው የመምራት ብቃት ከሌለው ወንድ ስለሆነ ብቻ ይመራል ማለት ነው? አይደለም፡፡ አስገዳጅ ሁኔታዎች የሚፈጥሩት ሂደትና አካሄድ ሊኖር ይችላል። ሆኖም የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትና አመራር እንዲሄድበት የተተለመለት ትልም አለ።

አንዳንድ ባህሎችና ሃይማኖቶች በሴቶች ላይ ድርብ ወይም የተለየ ጭቆና መረብ ይጥላሉ፡፡ በክርስትና መሠረታዊ የፆታዎች እኩያነት ከፆታዊ ሚና ጋር አለ። ገላ. 3፥28 "አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።" ሲል፥ ወንድም ሴትም የለም የሚለው ድነትንና የአካል አንድነትን የተመለከተ እንጂ ሚናና አገልግሎትን የመለወስ አይደለም፡፡ ክርስቲያን ሲኮን ወንድና ሴት መሆን ቀረ? አልቀረም። አይሁድና ግሪክ የሚባሉ ሰዎች ወይም ባሪያና ጨዋ የሚባሉ መደቦች ተደመሰሱ? አልጠፉም፡፡ የእግዚአብሔር ልጅነታችንን ግን እነዚህ ነገሮች አይገድቡትም። ባርነትም አልቀረም፤ ክርስቲያን ባሪያዎችም ኖረዋል፡፡ እንደዚያው ወንድና ሴትነትም አልቀረም። ተመሳሳይ አሳብ በቆላ. 3፥11ም እናገኛለን፤ "በዚያም የግሪክ ሰው አይሁዳዊም የተገረዘም ያልተገረዘም አረማዊም እስኩቴስም ባሪያም ጨዋ ሰውም መሆን አልተቻለም፥ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፥ በሁሉም ነው፡፡"

ስድስት፤ የእንስታዊ ንቅናቄ ጅማሮ

ወደ እንስታዊ ንቅናቄ ታሪክ ስንመጣ፥ በዚህ ተከታታይ ጽሑፍ መግቢያ ላይ ጅማሮው 1960ዎቹ መሆኑን አመልክቻለሁ። እንስታዊ ስነ መለኮትም አብሮት የተጀመረ ነው፡፡ ከዚያ በፊት የሴቶችና የሴትነት ወይም እንስታዊ እንቅስቃሴዎች ነበሩ። እንስታዊ እንቅስቃሴ በአጭሩ ወንዶች ያሏቸውን መብቶችና ሥልጣኖች ሁሉ ከወንዶቹ እኩል ሴቶቹም መደሰት አለባቸው የሚል ትግል ነው፡። እንስታውያን ዓይነታቸው ብዙ ነው፤ አንዳንዶቹ፥ ለምሳሌ፥ ጽንፈኛ ወይም ስር-ነቀል እንስታውያን (radical feminists) ከወንዶች እኩል ብቻ ሳይሆን ወንዶችን የበታች ለማድረግ ወይም ወንዶች አላስፈላጊ እንደሆኑ ለመቁጠር ይራመዳሉ፤ ይታገላሉ፡፡ አላስፈላጊነታቸው ወሲባዊ ሩካቤንም ይጨምራል፡፡

ከ1960ዎቹ በፊትም ነበሩ ስላልኩ ጥቂት ወደ ኋላ ፈቀቅ ልበል። ወደ ተሐድሶው ዘመን ስንሄድ ቀድሞውኑ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተዋፍት ሴቶች የሰይጣን መሳሪያ ተደርገው ይታዩ ነበር። ሔዋን የመጀመሪያዋ የሰይጣን ማታለል ሰለባ እንደሆነችው ማለት ነው። ይሁን እንጂ በካቶሊክ ማኅበራት የሴቶች ወይም የደናግል ገዳማት ተገድመው በተቋም ደረጃ አገልግሎት ሲሰጡ ኖረዋል። በአዲሱ የእንስታዊ ንቅናቄ ውስጥ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከቀደምት አራማጆቹ መካከል ናት፡፡

የተሐድሶው አራማጆች ሴቶች የሰይጣን መሳሪያ የመሆናቸውን መፈክር ከማሰማት በተቃራኒ ሴቶች ከወንዶች እኩል የእግዚአብሔር አምሳልና ምሳሌ መሆናቸውንና የአማኞችን ሁሉ የንጉሥ ክህነት (1ጴጥ. 2፥9) አስተምረዋል። በካቶሊክ ሥርዓት የካህንና የመደዴ ወይም ተርታ ሰው ልዩነት የገነነ ነው። ከተሐድሶው በኋላ ባሉት ክፍለ ዘመናት በተለይ በአውሮጳ በስፋትም ባይሆን ሴቶች ከወንዶች እኩል ተማሪ ቤት ገብተው መማርም ጀመሩ፡፡ ተሰደው ወደ አሜሪካ ከመጡት መካከል በሜተዲስት እና ኩዌከር ማኅበራት ሴቶች ማስተማርና መስበክን ጨምሮ የኃላፊነት ቦታዎችንም መሳተፍ ችለው ነበር።

የ1920ቹ የምዕራቡ ዓለም የሴቶች ንቅናቄዎች ይዘታቸው ፖለቲካዊ ሆኖ የመብት ጥያቄ፥ በተለይም የፖለቲካ ምርጫ ላይ ድምጽ መስጠት የመቻል (suffrage) ንቅናቄ ነበር። ይህ መልክና ቅርጽ ሲይዝና ሴቶችም መምረጥ ብቻ ሳይሆን በታችኞቹ እርከኖች ለምርጫ መወዳደርም ሲጀምሩ ታላቁ የምጣኔ ሀብት ቀውስ ዓለምን፥ በተለይም አሜሪካን ደቆሰ። ሥራ አጥነትም ሲንሰራፋ ሴቶች የወንዶችን ሥራ እንዳይሻሙ በሚል ሰበብ የእኩልነቱ ትግል ተቀዛቀዘ። ያንን የዳሸቀ ኢኮኖሚ ተከትሎ 2ኛው የዓለም ጦርነት መከሰት ወንዶች ለጦርነት ሲሰለፉ ሴቶች የወንዶቹንም ሚና ጨምረው የቤት ተግባርን መወጣት ሲጀምሩ የሴትነት ወይም እንስታዊ ስነ ልቡና እንደገና መጎልበት ጀመረ።

2ኛው የዓለም ጦርነት አብቅቶ የምጣኔ ሀብት እድገት ማንሰራራት ሲጀምር ሴቶች ቀድሞውኑ መራጭነትን ተቀዳጅተዋል። በቀጣዮቹ ዐሥርቶች በ1940ዎቹና 50ዎቹ ቅኝ አገዛዝና ኢኮኖሚያዊ ኢምፔሪያሊዝም፥ ኮሚኒስታዊ መስፋፋትና በአሜሪካ የጥቁሮች የመብት ጥያቄ ውስጣዊ ማዕበል ሆነው ቆይተዋል። ይህን ተከትሎ የአርነት ንቅናቄዎችና አብሮትም የአርነት ስነ መለኮት (Liberation Theology) ብቅ አለ። በ1960ዎቹ የአውሮጳ ቅኝ አገዛዝ ቀንበር ከአፍሪቃ መሰባበር ጀመረ።

እንስታዊነትን ስናጤን፥ አብዛኞቹ አቀንቃኞቹ የተገኙበትንና ስነ መለኮቱ ወደ ሌሎቹ የዓለማችን ክፍሎች ከመናኘቱ በፊት የመነጨበትን አገረ አሜሪካን ስንቃኝ፥ 1960ዎቹ በአሜሪካ የሂፒ ባህል የሚባለው፥ በተለይ በወጣቱ የማኅበረ ሰቡ ክፍል ስር ሰደደ። የአደንዛዥ ዕጾች፥ ወግ አጥባቂነትን መጥላት፥ በቡድን ወይም በጋርዮሽ መኖር፥ የወሲብ አብዮት፥ አፍቅሮተ ኮሚኒዝም፥ መንግሥትን የመቃወምና ብሎም የመዳፈር ወኔ መገንገን ጀመሩ፡፡ እንስታዊ ስነ መለኮትም በዚህ ወግ አጥባቂነትን የመግፋት፥ አርነትን የማሸብረቅ፥ ኮሚኒስታዊ የእኩልነት ትርክትን የማድነቅ ሂደት ውስጥ ነው የተወለደው፡፡

በነዚህ ዓመታት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የጉዳዩ አድናቂና አቀንቃኝ ሆነች። በ1963 የሮማው ጳጳስ ዮሐንስ 23ኛ የሴቶች እኩልነት ከማጀት እስከ አደባባይ ብቻ ሳይሆን እስከ ቅስናም ቢሆን የሚል አሳብ አካፈለ። ይህ የተባለውና የተጻፈው ከዋናው ፓትርያርክ ለጳጳሳት በሚጻፍ የውስጥ ደብዳቤ (encyclical) ነው። በ1966 ደግሞ የሴቶች ተሳትፎ በማኅበረ ሰቡ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያን ተልእኮ (apostolate) ውስጥም የጎላ ሚና መጫወት እንዳለበት ተነገረ። (Documents of Vatican II - 1966)። ካቶሊካዊው ድጋፍ ለእንስታዊ ስነ መለኮት ብቻ ሳይሆን፥ ጥቂት ቀደም ሲልና በዚሁ ተመሳሳይ ዘመን ለተከሰተው የአርነት ስነ መለኮትም ጭምር ነበር። እንስታዊነት ዘርፉ ብዙ ነው። ዋናዎቹ ለዘብተኛ፥ ጽንፈኛ፥ ፖለቲከኛ፥ እና ሃይማኖተኛ ናቸው፡፡

ሰባት፤ የእንስታዊ ንቅናቄ እድገት

“እንስታዊነት ዘርፉ ብዙ ነው፡፡ ዋናዎቹ ለዘብተኛ፥ ጽንፈኛ፥ ፖለቲከኛ፥ እና ሃይማኖተኛ ናቸው።‛ በማለት ነበር ያለፈውን ክፍል የጨረስኩት። እንስታዊነት ዘርፈ ብዙነት ብቻ ሳይሆን ዙር በዙር የሚሄድ ቀጣይነት ያለው ንቅናቄም ነው። እስካሁን አራት የእንስታዊነት ዙሮች ወይም ወጀቦች (four waves of feminism) ተከስተዋል፤ አሁን አራተኛው ላይ ነው ያለው። የመጀመሪያው ከዚህ በፊት ያየነው የሴቶች መብቶችን፥ የሥራ ገበታ እኩልነቶችን፥ የፖለቲካ መራጭ ድምጽንና የተመራጭነት መብቶችን የያዘው እስከ 20ኛው ምዕት ዓመት አጋማሽ (1950ዎቹ) የነበረው ነው፡፡

ሁለተኛው ወጀብ ወይም ማዕበል የ1960ዎቹ ነው፡፡ ወሲባዊነት የታዘለበት ከፆታዊነት ይልቅ ግላዊነት የተላበሰ፥ ከቀላሉ ከእኩል ክፍያና እኩል መብት እስከ ማን አለብኝነት እርምጃ የተራመደ ነው። ማን አለብኝነት በተለይ ከወሲባዊ የአካል መብት ጋር የሚያያዝ ነው። የወሊድ ቁጥጥር የውርጃ ነጻነት፥ “የማንም አይደለሁም፤ የራሴ ነኝ!‛ የሚል አካሄድ ነው። በነዚያ ዓመታት ብዛት ያላቸው የወሊድ መከላከያዎች ገበያ ላይ ውለዋል፤ አንዳንዶቹ በቂ ጥናትና ሙከራም ያልተደረገባቸው ሳይሠሪ እየቀሩ ብዙ አካለ ጎዶሎ ሕጻናት ተወልደዋል። ይህ ማዕበል ከ1960ዎቹ እስከ ክፍለ ዘመኑ ማብቂያ የደረሰው ነው። እንስታዊ እንቅስቃሴ በደማቁ ቅርጽ የያዘውም፥ እንስታዊነት ሲታሰብ ጅማሮው የሚጠቀሰውም ከዚህ ነው፡፡

ሦስተኛው ማዕበል ከ1990ዎቹ የሚጀምርና እስከ 2010ዎቹ የዘለቀ በወጣት ሴቶች ዙሪያ የሚሽከረከር፥ በፆታ ትርጉምና ትርጉሙን የማደብዘዝ ሂደት ላይ ያተኮረ፥ Wokeism እና ኋላ የተጨመረው Intersectionality ወይም Critical Race Theory የታከሉበት፥ አሁንም ከወሲባዊ ነጻነት ጋር የተያያዘ ሆኖ የፆታዊነት ጥያቄ ሆነ። በ2ሺህ መጀመሪያ አስታውሳለሁ አመልክባት በነበረችው ቤተ ክርስቲያናችን ፆታዋን የቀየረች ወንድ የሆነች ሰው አባልነት ጠይቃ ጉዳዩ ኮሚቴ ተመሥርቶ እንዲያጠናው ተደርጎ ነበር። እኔ በጊዜው ከተማችንን እና ቤተ ክርስቲያኒቱንም ትቼ የምሄድበት ጊዜ ስለነበረ ባለ ሁለት ገጽ ደብዳቤና ማሳሰቢያዬን ሰጥቼ ነበር የሄድኩት፡፡ ነጥቡ ግዙፍ የሆነው ጉዳዩ ቀጣይ ስለሆነ ነበር። ደግሞም ቀጣይ ሆኗል፡፡

አራተኛውና አሁን ያለንበት የእንስታዊነት ማዕበል፥ እንስታዊነት (feminism) ከመባል ይልቅ ልውጥ ፆታዊ እንስታዊነት (Trans-gender feminism) የሚባል ሆኗል፡፡ ይህኛው ሴቶችን ራሳቸውን እያስወገደ ያለና የማስወገድ ውስጣዊ አቅምም ያለው ንቅናቄ ነው። ወንዶች ሴቶች እየሆኑ ሴቶችን እያለፉና እየበለጡ እየመጡ ናቸው። በአሁኑ ጊዜ ሴት የሆኑ ጡንቻማ ወንዶች በወንድ ወይም ተባእታዊ ተክለ ሰውነት ከሴቶች ጋር በመወዳደርና በቀላሉ በማሸነፍ ብዙ የሴቶች እስፖርቶችን ሬከርድ ሰብረው ባለ ሬከርድ (ወይም ባለ title) ሆነዋል። የሴትነት መለኪያም እየሆኑ ያሉት እነዚህ ሆነዋል። ጽንፈኛ እንስታውያን ወንዶች አላስፈላጊ ናቸው ለወሲብም ጭምር እስከማለት ሲሄዱ፥ ልውጥ ፆታውያን ደግሞ ይህንን አስከንድተውታል። ሴቶች ራሳቸው በሴቶች አላስፈላጊ እየሆኑ ወይም ወንዶች ቅርጻቸውን (ማለትም ፆታቸውን) ቀይረው እንስታዊነትን እየተቀዳጁ ነው፡፡ ቀጣዩ ማዕበል ምን እንደሚሆን ወይም ምን እንደሚመስል ማን ያውቃል?

እንስታዊነት ዘርፈ ብዙ መሆኑንና ዋናዎቹ ለዘብተኛ፥ ጽንፈኛ፥ ፖለቲከኛ፥ እና ሃይማኖተኛ መሆናቸውን በመጥቀስ ነው የጀመርኩት፡፡

ለዘብተኛ እንስታዊነት ሴቶች በአደባባይ ሳይሆን በቤታቸው ተገቢ ሚናቸውን እንዲወጡ ፈላጊ ናቸው። በአብዮትና በግብታዊነት ወይም በስር ነቀል ለውጥ ሳይሆን በሂደትና አስፈላጊ ብቻ የሆኑ እኩልነቶች የመካፈል ጉዞ ነው። ወንዶችን በማግለል አያምንም፡፡ እንዲያውም የእንቅስቃሴው አባላት ለሴቶች መብት የሚሟገቱ ወንዶችም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ወሲብ በአጠቃላይ በማኅበረ ሰቡ ዘንድ ተበላሽቷል? ወይስ አልተበላሸም ብሎ ያንን ለማረቅ ከመጣር አንጻር እንጂ ፆታና ወሲብ እንደ ሞክሼ መታየት ወይም እንስታዊነት ከወሲባዊነት ጋር ተቆራኝቶ መታየት የለበትም ባይ ንቅናቄ ነው።

ለዘብተኛ እንስታዊነት መካከለኛውን ስፍራ በመምረጥ፥ ባለማፈንገጥ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ፥ በተለይም ባህላዊ ጎጂ ተጽእኖዎችን በመቅረፍ ላይ ያተኩራል። ለምሳሌ፥ የሴቶች ግርዘት፥ የወሲብ ሸቀጥነት የወሲብ ትራፊክ፥ በመንፈሳዊ መሪዎች በሴቶች ላይ በተለይ የሚደርሱ ወሲባዊና ሌሎችም ጥቃቶች፥ በእስርና ማረሚያ ተቋማት ይበልጥ ችግረኞች ሴቶች ናቸውና እነዚህን ችግሮች መቅረፍ፥ ወዘተ፥ ላይ የሚያተኩር ንቅናቄ ነው፡፡

ስምንት፤ ፖለቲካዊ እንስታዊነት

ባለፈው ክፍል ፖለቲካዊ እንስታዊነትን አይተናል። ፖለቲካዊ እንስታዊነት በርዕዮት ግራ ዘመም ወይም ማርክሳዊ ሌኒናዊና በቀለኛ እንስታዊነት መሆኑንም በትንሹ አይተናል።

ፖለቲካዊ እንስታዊነት ከእንስታዊ ስነ መለኮት አንጻር ሲታይ በመጽሐፍ ቅዱስ በዘፍ. 3፥16 በዔድን ገነት የተበየነው የፈቃድ ወደ ባል መሆን እንደ ቀንበር የታየበትና ከዚያ ለመላቀቅ የተደረገ የፆታዊ አርነት ንቅናቄ ወይም እንቅስቃሴ “ክርስቲያናዊ ወይም ሕዝባዊ አስተምህሮ ነው።

በአንዳንድ እናታዊ (matriarchal) ማኅበረ ሰቦች በቀር በብዙ ባህሎች ውስጥ ሴቶች በእርግጥም ድርብ ጭቁኖች መሆናቸው እውነት ነው። ይህ ድርብ ጭቆና አንዳንድ የንቅናቄው አራማጆች ከተጨቋኝነት ነጻ መውጣትን ብቻ ሳይሆን እንዲያውም አልፎ ወደ ጨቋኝነት የመራመድንና የመበቀልን ንጽረተ ዓለም እንዲያዳብሩ አድርጎአቸዋል፡፡ ልክ በሶሻሊስታዊ አብዮቶች የወዛደሩ መደብ የቡርዧውን መደብ እኩልነት አልበቃ ብሎት እንዳዋረደውና እንደተበቀለው የመሰለ አካሄድ ነው።

ይህ የአርነት እንስታዊ ንቅናቄ የፖለቲካ እንስታዊ ንቅናቄ ተብሎም ይወሰዳል። በቅርጹም በይዘቱም ሕዝባዊና ፖለቲካዊ ነው። የሥራ እኩልነት፥ የመምረጥና መመረጥ ብቻ ሳይሆን የሥልጣንና ቁልፍ ቦታዎችንም መጋራትና መያዝ የንቅናቄው ዘርፎች ናቸው፡፡

የ1960ዎቹ የአሜሪካ የሂፒ ንቅናቄ ገጽታ ወጣቱና ከወጣት አለፍ ያለ ዕድሜ ውስጥ፡ የሚገኘው የማኅበረ ሰቡ ክፍል የነባር ባህላዊ፥ ሕዝባዊና፥ ማኅበራዊ እሴቶች ታቃውሞ፥ የመንግሥትና መንግሥታዊ ተቋማት ተቃውሞ፥ የምሥራቅ ሃይማኖቶች፥ የአደንዛዥ ዕጾች፥ የደቦ ወይም የወንፈል አብሮ መኖር፥ ወሲባዊ አብዮት፥ ማርክሳዊ ሌኒናዊ ርዕዮት፥ ወዘተ፥ አየሩን የሞሉበት ጊዜ ነበረ። ማርክሳዊና ሌኒናዊው አብዮት የተለየ ትኩረት በብዙ አገሮች ተቀዳጀ።

ማርች 8 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ሆኖ መታሰብና በተለይ በሶሻሊስቶቹ አገሮች መከበር የጀመረውም በ1960ዎቹ ነው። በብዙ ሶሻሊስት አገሮች የሴቶች በማኅበራት መደራጀት በአብዛኛው ፖለቲካዊ ይዘት የተላበሰ ነው። በአገራችንም የሴቶችን ጉዳይ በተለይ የሚያራምድ አኢሴማ (የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር) ሲቋቋም የሴቶች የቀድሞ ሁኔታ የተሰጠው ስያሜ፥ “ድርብ ጭቁን' የሚል ነው። አብዮቱም የሴቶች አርነት ወላጅ ሆኖ ታየ፡፡

በእርግጥም የሴቶች ሁኔታ በብዙ አገሮችና ባህሎች፥ በተለይም ባላደጉትና ኋላ ቀር በሆኑት ዘንድ የከፋ ነው። ይህንን ኋላ ቀር ማኅበራዊ ጉዳት ለመቅረፍ ሶሻሊስታዊው ንቅናቄ የሄደበት እርምጃ መጠነኛ ለውጥ ቢታይበትም ርዕዮተ ዓለሙ የተመሳቀለ መሆኑና የሴቶች ሁኔታ መሻሻል ሶሻሊዝም ባይኖርም ምጣኔ ሀብታዊና እውቀታዊ (አካዳሚያዊ) እድገት ሊፈጥረው የማይችለው አስመስሎ ማሳየቱ ስሕተት ነው። ቆይቶ እንደታየውና ሶሻሊስታዊው ንቅናቄ ሲፈረከስ ገሃድ እንደወጣው ይህ ፖለቲካዊ እንስታዊነት ያፈራው ፍሬ ከለዘብተኛ እንስታዊነት ብዙም ያለፈ አይደለም। ኑሮን ማሸነፍ መቻል ትልቁ ጥያቄ ሆኖ መኖሩ እንደተጠበቀ ግን የተለየ ግፍና ጡር በሴቶች ላይ እንዳይደረግ ልዩ ልዩ መጠበቂያዎች ተደርገዋል። ሌሎቹ ሁለቱ ስር ነቀል እና ሃይማኖታዊ እንስታዊነቶች ናቸው፡፡

ዘጠኝ፤ ጽንፈኛ ወይም ስር ነቀል እንስታዊነት

ባለፈው ክፍል ፖለቲካዊ እንስታዊነትን አይተናል። ፖለቲካዊ እንስታዊነት በርዕዮት ግራ ዘመም ወይም ማርክሳዊ ሌኒናዊና በቀለኛ እንስታዊነት መሆኑንም በትንሹ አይተናል። ጽንፈኛ ወይም ስር ነቀል እንስታዊነት ደግሞ ለዘብተኛውንም፥ ፖለቲካዊውንም አጀንዳ ያነገበ ሆኖ ሁሉንም የሚያጦዝ እንስታዊነት ነው። ሴቶች ከውንዶች ጋር እኩል ብቻ ሳይሆኑ የበላይ ናቸው የሚል ቅኝት ያለው ዜማን የሚያቀነቅን ንቅናቄ ነው። ለዘብተኛው እንስታዊነት ለሴቶች መብት እስከተሟገቱ ድረስ ወንዶችም የንቅናቄው አካል መሆን ይችላሉ የሚል ሲሆን ይህኛው ወንዶች አላስፈላጊ ናቸው የሚል ነው፡፡

የጽንፈኛ እንስታዊነት ወንዶችን የማውገድ ወይም አላስፈላጊ የማድረግ አካሄድ እስከ ወሲባዊ ተጋብሮና ተራክቦም የሚደርስ ነው። ወንዶች ሴቶችን የወሲብ መሣሪያ ወይም ዕቃ አድርገው የሚጠቀሙ ፆታዎች ስለሆኑ ወንድ አልባ ወሲብን የመደገፍና የማራመድ ተልእኮን አንግበው የሚጓዙ ናቸው። ይህ ግብረ ሰዶምን የማስፋፋት ንቅናቄ አንድ ፈርጅ ነው። በዚህ ጉዳይ Germain Greer የተባለች ከእንስታዊነት ንቅናቄ አቀንቃኞች አንዷ፥ The Female Eunuch በተባለ መጽሐፏ ወንዶች ሴቶችን የወሲብ መጠቀሚያ በማድረግ ፆታዊ ወይም ወሲባዊ ብዝበዛን የሚፈጽሙ በዝባዦች መሆናቸውን በማብራራት የወንዶች ተጠቂና መጠቀሚያ ከመሆን ወሲባዊ ተራክቦን በተመለከተ ከተመሳሳይ ፆታ ጋር ግንኙነት መፍጠር የተሻለ አማራጭ ነው ትላለች።

የጽንፈኛ እንስታዊነት ሌላ ገጽታ ሴቶች የወንዶች ጥገኛ የሚሆኑት በምንም ተፈጥሯዊ ማነስ ሳይሆን በእርግዝናና በወሊድ ምክንያት መሆኑን በሴቶች ስነ ልቡና ውስጥ ማስረጽ ነው። ከዚህ የተነሣም አለማርገዝና አለመውለድን ማበረታታት፥ እንዲሁም ከተረገዘ አለመውለድን ወይም ማስወረድን ማበረታታት የንቅናቄው ፈርጅ ነው፡፡ Shulamith Firestone የተባለች የስር ነቀሉ እንስታዊ ንቅናቄ እውቅ ጸሐፊ The Dialectic of Sex በተባለ መጽሐፏ ይህን ጉዳይ በስፋት ጽፋዋለች። እነዚህን አመለካከቶች በሴቶች ውስጥ ማስረጽ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካዊ እንስታዊነት አማካይነት እና የlobbying ወይም ባለ ሥልጣኖችን በማሳመን ፖሊሲዎችን ማስቀረጽንም በስፋት ያደርጋሉ፡፡

ጽንፈኛ እንስታውያን የPro choice (ውርጃን ሕጋዊ የማድረግ) እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም ተሟጋቾች ናቸው። ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱም ሴቶች ይህንን አመለካከታቸውን ያዳበሩት የእንስታዊነት ንቅናቄ በተጀመረበት በ1960ዎቹ ሲሆን መጽሐፎቻቸው የተጻፉት በ1970ዎቹ መጀመሪያ ነው። የጽንፈኛ እንስታዊነት ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱም ነጥቦች ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊና ሰይጣናዊ ለመሆናቸው እንደ ክርስቲያን ብዙ መመርመር አያሻንም። መብዛትና መባዛት ከጅምሩ የእግዚአብሔር አሳብ መሆኑ በዘፍ. 1 እና 2 ተጽፎአል። የሰዶማዊነት ኃጢአት ደግሞ ከሰዶምና ገሞራ ቅጣት ጋር ተያይዞ ተጽፎአል፤ ዘፍ. 18 እና 19። በተጨማሪ 1ነገ. 14 እና 15፤ 2ነገ. 23፤ ሮሜ 1፤ 1ቆሮ. 6 ይህን ርኵሰት ይናገራሉ፡፡

ሴት በተፈጥሮ ከወንድ በምንም የማትተናነስ መሆኗን አበክረው ቢናገሩም ሴት በብዙ ረገድ በእግዚአብሔር ልዩ ሆና እንደተፈጠረች አይቀበሉም። አንዳንዶቹ ሴት የሆኑ ወይም ፆታቸውን ወደ ወንድ የቀየሩ ትራንሶችን በማድነቅ ቢያዩም፥ ብዙዎች እየደነገጡ ይታዘቧቸዋል። ቀደም ሲል ካየናቸው አራቱ የእንስታዊነት ማዕበሎች ወይም ወጀቦች አራተኛው የሆነው የልውጥ ፆታዊ እንስታዊነት (Trans-gender feminism) የእንስታዊነት መልስ እየመሰላቸው፥ ከመልስ ይልቅ ግራ አጋቢ ጥያቄም እየሆነባቸው ነው፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ራሳቸውም ሊመልሷቸው እየተቸገሩባቸው ያሉ የንቅናቄው ገጾች ናቸው፡፡

አሥር፤ ሃይማኖታዊ እንስታዊነት

ባለፉት ክፍሎች እንዳየነው፥ እንስታዊነት ኅብሩና ፈርጁ ብዙ ነው። ወደ ሃይማኖታዊ እንስታዊነት ስንመጣ ከሃይማኖታዊው ክልል ውጪ ከለዘብተኛው እስከ ጽንፈኛው እንዳለው ሁሉ እዚህም እንደዚያ ነው፡፡ በታሪክ ውስጥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሴቶች ምንም ስፍራ ተነፍጎአቸው ብቻ ሳይሆን፥ ከሔዋን ጀምሮ ሴቶች የሰይጣን መጠቀሚያ፥ የፈታኝ መሳሪያ፥ የውድቀት ምንጭ እየተደረጉ የኖሩባቸው ዘመናት አያሌ ናቸው፡፡

በአንጻሩ ደግሞ በወንዶች ላይ ለመሠልጠን ብቻ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር ጨቋኝና ጨቋኝነቱም በተባዕታዊ ፆታ የተገለጠ በመሆኑ እግዚአብሔርን ወደ እንስታዊ የመቀየር አዝማሚያም የታየባቸው ሂደቶች ኖረዋል። “በሰማይ የምትኖር አባትእናታችን ሆይ" መባል አለበት ብለው የተከራከሩም ኖረዋል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር በእንስታዊ ስሜቶች የተገለጠባቸውን ቦታዎች ለምሳሌ፥ ርኅራኄ፥ አዛኝነት፥ ተሸካሚነት፥ ወዘተ፥ በመውሰድ እግዚአብሔርን እንስት አምላክ (Goddess) አድርጎ መጥራትና እንስታዊ ተውላጠ ስሞችን መጠቀም የጀመሩ ኖረዋል፡፡ ይህ ሃይማኖታዊ ቀለም የተቀባ ጽንፈኛ እንስታዊነት ነው።

በሁለቱ የተራራቁ አመለካከቶች መካከል የሚገኘው ክርስቲያናዊው እንስታዊ ንቅናቄ በአንዳንዶች ዘንድ “ወንጌላዊ እንስታዊነት" የሚባለውና በመጽሐፍ ቅዱስ ዙሪያ የሚያጠነጥነው ነው። ሃይማኖታዊ እንስታዊነት ሰፊ በመሆኑ እዚህ የማወሳው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ክርስትናን ብቻ ነው። ይህኛው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምራቸው እውነቶች እንደተጠበቁ ሆነው፥ ከቃሉ በወጣ፥ ባፈነገጠ መልኩ በወንድ የበላይነትና በባህል ምክንያት የተጫኑ ቀንበሮች መነሣት አለባቸው የሚል ንቅናቄ ነው። ስለ ባህልና እንስታዊነት ቀደም ሲል ተመልክተናል። በባህሎች ውስጥ ብቻ ሳይሆን በቃሉ ውስጥም የወንዶች ሚና ምንነትን በትንሹ አይተናል። ይህ ጽሑፍ ሁሉን በትንሽ በትንሽ በማሳየት፥ የማያውቁ በጥቂቱ እንዲያውቁ፥ በስፋት የሚሠሩ ደግሞ እንዲንደረደሩበት ነው።

ክርስቶስ የሴቶችን አርነት በተግባር ያሳየ ጌታ ነው። ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ሴቶች ነበሩ፡፡ የአገልግሎቱ ደጋፊዎችና የትንሣኤው ቀዳሚ ምስክሮችም ሴቶች ነበሩ። በዚህ ረገድ፥ የጌታ አገልግሎት የአይሁድን ባህላዊና ልማዳዊ እይታ ተገዳድሮአል። ጌታ ሲያስተምር፥ ቃሉን የሚሰሙና የሚጠብቁ፥ የአባቱን ፈቃድ የሚያደርጉ እነዚህ ወንድሞቹ፥ እኅቶቹና እናቶቹ እንደሆኑ ተናገረ፤ ማቴ. 12፥50፤ ማር. 3፥35። ይህ ትልቅና ድንቅ የሆነ ማቅረብ ነው። ከጌታ ደቀ መዛሙርት መካከል በግልጽ ሴቶች ይኑሩ እንጂ ጌታ ከሴቶች መካከል ሐዋርያት እንዲሆኑ አልመረጠም፤ አልላከም፡፡ ይህ ከወንጌሉ ነው።

ወደ ሐዋርያት ሥራና ወደ መልእክቶች ስንመጣም ተግባራዊ አገልግሎቱ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ጸጋና ፆታ በሚለው ክፍል እንዳየነው ወንዶችም ሴቶችም የአካሉ ብልቶች ናቸው፤ ብልቶችም ሁሉ ተግባር አላቸው። አስተዳደር ወይም አገዛዝና ኃላፊነት ደግሞ ተለይቶ ለወንዶች የተሰጠ መሆኑም በግልጽ ታይቶአል፡፡ ሐዋርያቱ ከጌታ የተቀበሉትን አድርገዋል፤ ቀጣዮቹ አብያተ ክርስቲያናትም ከሐዋርያቱ ያዩትንና የተቀበሉትን አድርገዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ታሪክም ይህን በጉልህ ጽፎታል፡፡

በአንዳንድ የአዲስ ኪዳን ከተሞችና አብያተ ክርስቲያናት፥ ከባህሉም አንጻር የሴቶች ሚና ተጠቅሶ ይህን እንዲያደርጉ፥ ያንን እንዳያደርጉ የተጻፈባቸው ምንባባት የባህልና የወግም፥ የሕግ ወይም የደንብና የሐዋርያት ትእዛዝም የተቆራኘባቸው ናቸው። በıቆሮ. 14፥34-35 በማኅበር ዝም ማለትና መገዛት ለቆሮንቶስ ብቻ ነው ካልን፥ በኤፌሶን አይሠራምና በኤፌሶን የማይተረጐም ልሳን መነገር ይቻላል እንደ ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲጻፍ ያደረገው መንፈስ ቅዱስ እኛን ታሳቢ ሳያደርግ እንዲጻፍ አላደረገም። ቀበሌያዊና ባህላዊ ተጽዕኖዎች መኖራቸው እውነት ሆኖ እየተላለፈ ያለው መንፈሳዊ አኗኗርና አገልግሎት ጉዳይ መሆኑም መረሳት የለበትም። ሴቶች ጭቁኖችና የበታቾች አለመሆናቸውን ጳውሎስ ለኤፌሶን አማኞች ሲጽፍ አመለከተ፤ በኤፌ. 5፥22 "ሚስቶች ሆይ፥ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤" ከማለቱ በፊት በቁጥር 21 "ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ።" አለ። አንዷ ለሌላው ማለት ነው፤ አንዱ ለሌላዋም ማለት ነው፡፡

በገላ. 3፥26-28 በክርስቶስ ያመኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውና፥ ከክርስቶስ ጋር የተጠመቁ ወይም አካሉ የሆኑ እርሱን መልበሳቸውን ጽፎ፥ "አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።" ብሎአል። ይህ ሃይማኖታዊ እንስታውያን ወንድና ሴት ብሎ ልዩነት እንደሌለ የሚጠቅሱት ምንባብ ነው። እንደሚጠበቀውም የሚያተኩሩት፥ “ወንድም ሴትም የለም' የሚለው ብቻ ላይ ነው። አይሁዳዊና የግሪክ ሰው፥ ወይም ባሪያና ጨዋ ላይ አይደለም፡፡ ዐውዱን ካልናቅነው በቀር ይህ ክፍል የፆታ ድምሰሳ ምንባብ አይደለም። በእግዚአብሔር ልጅነት ውስጥ እነዚህ ነገሮች አጋጅ አይደሉም ማለት እነዚያ ነገሮች የሉም ማለት አይደለም፡፡ አይሁዳዊና ግሪኩ ትውልዳቸው አልተሰረዘም። ክርስቲያን ባሪያ ጌታውን፥ 'እኔና አንተ እኩል ነን' ብሎ ባርነቱን አልሰረዘም። ባርነት ከቶም አልቀረም። ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት መልክ ነው የተቀየረው፡፡

ሴትና ወንድ ሲልም ፆታው አልቀረም፤ ሚናውም አልተቀየረም። የእግዚአብሔር ጸጋ አብሮ ወራሽ ተሆነ፡፡ ክፍለ ምንባቡ ስለ አብርሃም ልጅነትና የተስፋው ወራሽ ስለመሆን ነው የሚናገረው። በውስጣዊው ዘላለማዊው ማንነት አንድና እኩልታን የተጎናጸፍን ፍጡራኑና ልጆቹ ነን። ያ አካላዊ ማንነታችንን እና ፆታዊ ሚናችንን፥ በቃሉ መሠረት የተሰጠንን ጸጋና ሥልጣን ግን አይለውጠውም፡፡

ሴቶች የተሰጣቸውን ያንን ጸጋ ቃሉ በሚፈቅድላቸው መስመር ሊወጡት መንገድ የለም የሚሉ ሁከት ፈጣሪዎች ናቸው። ወንዶችም ወንዶች ስለሆኑ ብቻ ያገለግላሉ ማለት አይደለም። ጸጋና ፆታ በሚለው ክፍል እንዳየነው ሴቶች የማስተማር ጸጋ ካላቸው የሚያስተምሩባቸው እልፍ መንገዶች አሉ። “ከማን አንሳ ይህኛው መድረክ ይከለከላታል? ማለት መድረኩን ሳይሆን የፍላጎቱን ምንጭ ያመለክታል። ቃሉ እንደየባህላችንና እንደ ዘመናችን መልክ እያመሳሰልን የምናጠጋጋው ሳይሆን፥ ቃሉ ባህላችንን የሚቀርጽ መቅረጫ ነው፡፡

ቃሉ ባህላችንን እና ፍልስፍናችንን መምሰል የለበትም፥ በተቃራኒው ባህላችንና ፍልስፍናችን ነው ቃሉን መምሰል ያለበት፡፡ እንስታዊነት ለቃሉ መገዛት አለበት እንጂ፥ መጽሐፍ ቅዱስ እንስታዊነትን መምሰል ወይም ለመምሰል መልለወጥ የለበትም፡፡ ሴቶች የግድ በጉባኤ በመሪነት ላይ ሆነው ሰዎችን በመምራት ሳይሆን በውስን መልኩ ሴቶችን በመምራትና በማስተማር ማገልገላቸው ውበታቸው እንጂ ከቶም የበታችነት አይደለም። ከቶም።

በቤተ ክርስቲያንም የሴቶች መሪነትና ቅስና ንቅናቄ የተጀመረው ከጥንት ሳይሆን ከ1960ዎች የአርነትና እንስታዊነት ንቅናቄ በኋላ ነው። ተከትሎት የመጣው የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ሕጋዊ የመሆን ጥያቄም፥ ኃጢአቱ ቀድሞም የነበረ ቢሆንም ዘሩ የተዘራው በተለይ ከጽንፈኛ እንስታዊነት ጋር ተያይዞ ነው። ቤተ ክርስቲያን ሁሌም የማይለወጥ መሪ ቃል ያላት በዓለቱ ላይ የተመሠረተች አካል ናት እንጂ በየዘመናቱ በሚመጡ (እንስታዊ ንቅናቄንም በሚጨምር) ንቅናቄዎች የፊት አቅጣጫዋ የሚለዋወጥና በነፋስ የምትገፋ መርከብ አይደለችም። የእንስታዊነት ንቅናቄ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም፡፡

ተፈጸመ፡፡