መግቢያ
ይህ ዘመን ከመቼውም ይልቅ ሐሰተኛ ነቢያት የበዙበት ነው፡፡ ሐሰተኛ ነቢያትና የሐሰት አስተማሪዎች የሐሰት አባት ሰይጣን በዔድን ገነት ሔዋንን ካሳተባት ጊዜ ጀምሮ ነበሩ፡፡ እስከ ፍጻሜ ዘመናትም ይቀጥላሉ፡፡ በብሉይ ኪዳንም ነበሩ፤ በጌታ ዘመንም ነበሩ፤ በሐዋርያቱም ዘመን ነበሩ፡፡ ዛሬም በእኛ ዘመን በዝተው ይገኛሉ፡፡
ይሁዳ መልእክቱን በጻፈበት ዘመን ሐሰተኞች አሳሳቢ ሆነው ነበር። ይህ ችግር ይሁዳን የመልእክቱን ይዘት እስከማስቀየር ያደረሰው አሳሳቢነት ጉዳይ ነበረ። ስለዚህ ነው በቁጥር 3 ላይ፥ "ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ፡፡" ያለው፡፡
ዛሬም የሐሰተኛ ነቢያት ጉዳይና ብዛት አሳሳቢ ነው። ቅዱስ ቃሉ የሚያስተምረንም በመጨረሻው ዘመን ይህ አሳሳቢነት እንደሚቀንስ ሳይሆን እንደሚጨምር ነው። ጌታ ይህን አስተምሮአል። በማቴ. 7፥22 "በዚያ ቀን ብዙዎች፦ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል።" ብሎአለ። በማቴ. 24፥5 እና 11 "ብዙዎች፦ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ፤" ብሎአል። ሐዋርያው ዮሐንስም ከማሳሰቢያ ጋር፥ "ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን፡፡" "ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና።" ብሎአል፤ 1ዮሐ. 2፥18 እና 4፥1።
ይሁዳ ይህን አሳሳቢ ጉዳይ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ሲጽፍ ይህን አስተውሎአል፡፡ በጣም በግልጽ ቋንቋና በብዙ ምስላዊ ምሳሌዎችም አድምቆ ነው የጻፈው። ማስጠንቀቁ በእጅጉ አስፈላጊ ነበር። በዚህች አጭር ለግል ንባብም ለቡድን ጥናትም የተዘጋጀች ሐቲት ይህንን የይሁዳን አሳሳቢና አስጠንቃቂ አሳብ እንካፈል፡፡