የህይወት ቃል ህብረት Logo

ሰው ምንድር ነው?

'ሰው መንፈስ ነው፤ ነፍስ አለው፤ በሥጋ ውስጥ ያድራል' ለሚለው ስሕተት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምላሽ።

በ ዘላለም መንግሥቱ

መግቢያ

የዚህች መጽሐፍ መነሻ በ2017 ሜይ ወር የጻፍኩትና በዕዝራ የኢንተርኔት መጽሔት የበተንኩት፥ 'ሰው መንፈስ ነው? ወይስ ሰው ነው?' የሚል መጣጥፍ ነው። ያንን ጽሑፍ የጻፍኩት በጊዜው ይህ ትምህርት እየተነዛ ነበርና፥ ከበርካታ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠይቄ፥ አንድ የተጻፈ ነገር በእጃቸው እንዲኖራቸው በማሰብ ነው። የመጀመሪያውን ጽሑፍ ከጻፍኩ በኋላም በርካታ ጥያቄዎች በየጊዜው እየተጠየቅሁ አጫጭር ምላሾች ስሰጥ ቆይቻለሁ፡፡

የመጀመሪያው ጽሑፍ ተደራሾች ጥቂት ሺህ ሰዎች ብቻ ስለነበሩ፥ በማኅበራዊ ገጾች ማካፈል አስፈላጊ ስለመሰለኝ በቪድዮ በሰባት ተከታታይ ክፍሎች አዘጋጅቼ አቀረብኩት። ... ለቪድዮ ትምህርት ማስታወሻ ጽሑፎች ሳዘጋጅ ቀድሞ በነበረው ጽሑፍ በብዙ ጨምሬበት ስለነበረ፥ ደግሞም በየጊዜ የመለስኳቸው ጥያቄዎችም እየተጨመሩበት ያ የመጀመሪያው መጣጥፍ ስለዳበረ በመጽሐፍ መልክ ቢቀርብ ሌሎችን ሊጠቅም እንደሚችል በማመን በዚህ መልኩ እንደገና ቀርቧል።

አንዳንድ ጥያቄዎች መልሳቸው ገሐድ ስለሆነ ሞኝ ጥያቄዎች ይመስላሉ። 'ሰው ሰው ነው? ወይስ መንፈስ ነው? ሰው ሰው ነው? ወይስ ሰው ወይስ እግዜር ነው?' ብሎ መጠየቅ ጅልነት ይመስላል። ምክንያቱም፥ ነገሩ ገሐድ ነዋ! ይሁን እንጂ፥ ጥያቄው እንዲጠየቅ ግድ የሚያደርጉ ነገሮች ሲፈጠሩ፥ ሰው ሰው አይደለም የሚሉ ስሕተቶች ሲናኙ፥ 'ሰው መንፈስ ነው፤ ሰው እግዜር ነው፤ እኔና አብ አንድ ነን፤ እኔ የእግዚአብሔር ዓይነት ነኝ፤' የሚሉ ስሕተቶች ሲነገሩ፥ እውነት እየመሰሉ ሲመጡ፥ ያኔ ሞኝ ጥያቄ መጠየቅ ግድ ይሆናል። 'ሰው መንፈስ ነው፤ ነፍስ አለው፤ በሥጋ ውስጥ ያድራል' ሲባል መስማት በወንጌላውያን አማኞች አካባቢ አዲስ አይደለም፡፡

ይህ የዘመናዊዎቹ የስሕተት ትምህርቶች ሁሉ እናት በሆነችው በአሜሪካ ውስጥ የተወለደ፥ እዚያው አሜሪካ ጡጦ ጠብቶ ያደገና በዓለም ዙሪያ የተወነጨፈ፥ ጥቂት ያልሆኑ ሰዎች በማደጎ የራሳቸው ልጅ ያደረጉት፥ በእውቀትም፥ ያለ እውቀትም፥ በስሕተትም፥ በመታለልም፥ የተቀበሉት፥ ያሳደጉት የስሕተት ትምህርት ነው። ይህ 'ሰው መንፈስ ነው፤ ነፍስ አለው፤ በሥጋ ውስጥ ያድራል' የሚባለው ነገር የቃለ እምነት ስሕተት የተጣረሰ ስነ ሰብእ ነው።

እንደዚህ ያለ አሳችና አሳሳች ነገር በመኖሩ፥ 'ሰው ምንድርን ነው?' ተብሎ መጥጠየቅ እና መጽሐፍ ቅዱሳዊው የሰው ማንነት ትምህርት መገለጥ አለበት፡፡ በአገራችን ይህንን ስሕተት ከመንዛት ጋር የሚቆራኙ ጥቂት ሰዎች ቢኖሩም ምንጩ ግን እነርሱ አይደሉም። ከማን ተኮረጀ? ከየት መነጨ? ያንንም እንመለከተዋለን፡፡

ሰው ምንድርን ነው?

'ሰው መንፈስ ነው፤ ነፍስ አለው፤ በሥጋ ውስጥ ያድራል' ወደሚለው ስሕተት እና ሐሳውያኑ ስለሚያቀርቧቸው አሳሳች አጠቃቀሶች ከመግባቴና ስሕተቱን ከመግለጤ በፊት ግን በቅድሚያ ትክክለኛውን፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ትምህርት በአጭሩ እንመልከት፡፡ ይህንን የምጀምርበትን ትምህርት መደምደሚያውም አደርገዋለሁ፡፡

ሰው ምንድርን ነው? በአጭሩ፥ ሰው ሰው ነው። ሰው ሲፈጠር ሰው፥ ሲኖር ሰው፥ ሲሞት ሰው፥ ከሞት በኋላም እንኳ፥ በትንሣኤም ሰው ሰው ነው። ካላወቅን እንወቅ፤ ሰው ሰው ነው። ሰው ከሌሎች አካላውያን ፍጡራን ሁሉ የላቀና የፍጡራኑ ሁሉ ቁንጮ የሆነ ፍጡር ነው። የፈጣሪያችን የእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ መሆናችን ብቻውን እንዴት የከበረ ነገር ነው! ያ ሰው ሆነን በመልኩ እንደ ምሳሌው መፈጠራችን ልካችን ነው፤ ያልበዛ፥ ያልተንዛዛ፥ ያላነሰ፥ ያልጎደለ ልካችን። ሰው መሆን በልካችን የተሠራ ማንነታችን ነው። ሰው ሲፈጠር ሰው ነው፤ በምድር ሲመላለስም ሰው ነው። ከውድቀት በፊት ሰው፥ ከውድቀት በኋላም የእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የሆነ ሰው ነው፤ ዘፍ. 1፥26-27፤ 2፥7፤ 9፥6። ከውድቀት በኋላም፥ ማለትም ከዘፍ. 3 በኋላም የሰውን ሰውነት ኃጢአት በከለውና ከአምላኩ ለየው እንጂ ሥሪቱ አልተቀየረም። የሰው ሰውነት ወይም ማንነት ዘላለማዊ ነው። ሰው ለዘመን ብቻ ሳይሆን ለዘላለምም ሰው ነው፡፡

ሰው መንፈስ ነው የሚሉ ሰዎች ከጅምሩ የተሳሳቱ መሆናቸውን የጅምሩ መጽሐፍ ያረጋግጥልናል፡፡ ሰው በውስጡ መንፈስ አለ እንጂ መንፈስ አይደለም። ሰው መንፈስ ቢሆን ኖሮ፥ ገና ሲፈጠር እግዚአብሔር፥ "መንፈስን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር" ይል ነበር። ቃሉ ግን፥ በዘፍ. 1፥26፤ "እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን [መንፈስን አይደለም፤ ሰውን] በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር..." ይላል። 'እንፍጠር' ያለው መንፈስን ሳይሆን ሰውን ነው። ቁጥር 27 ደግሞ፥ "እግዚአብሔርም ሰውን [መንፈስን አይደለም፤ ሰውን] በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፡፡" ይላል። በመልኩ የፈጠረው ሰውን እንጂ መንፈስን አይደለም፡፡ ወንድም ሴትም በመልኩ የተፈጠሩ ሰዎች ናቸው። ሰዎች ሰዎች ናቸው፤ መናፍስት ወይም መንፈሶች አይደሉም፡፡

በዘፍ. 2፥7 "እግዚአብሔር አምላክም ሰውን [መንፈስን አይደለም፤ ሰውን] ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም [መንፈስ አይደለም፤ ሰው] ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ፡፡" ይላል። ... ስለዚህ ሰው መንፈስ አይደለም፡፡ ነፍስም አይደለም፤ ሰው ሰው ነው እንጂ፡፡

ከዚህ ክፍል የምንረዳው ሰው ወይም የሰው አፈጣጠር በመጀመሪያ መንፈስ ተፈጥሮ ያ መንፈስ ሥጋ ሲመረግበት አይደለም፡፡ ሰው ከአፈር ተፈጥሮ ከዚያ ከእግዚአብሔር የሕይወት እስትንፋስ እፍ ሲባልበትና ሕያው ነፍስ ያለው ሲሆን ነው። ልብ እንበል፤ ነፍስም አልተባለም፤ 'ሕያው ነፍስ ያለው' ሆነ፡፡ ... ሰውን በተመለከተ፥ 'መንፈስ' የሚለው ቃል በዚህ ሰው በተፈጠረበት ታሪክ ውስጥ ጨርሶም የለም። ስለዚህ የመጀመሪያው ሰው አዳም፥ ምንድርን ነው? ሰው ነው። ... ሔዋንም ከሥጋ የተገኘች ሥጋ እንጂ መንፈስ አልነበረችም፡፡ ... "ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት..." ነው ያለው እንጂ፥ 'ይህች መንፈስ ከመንፈሴ ናት' አላለም፡፡ እግዚአብሔር በመጀመሪያ መናፍስትን አልፈጠረም፡፡ ሰዎችን ነው የፈጠረው፡፡

ሰው ሥጋና አጥንት አለው፡፡ ... መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውም። መንፈስ ሥጋና አጥንት እንደሌለው የነገረን ጌታ ኢየሱስ ራሱ ነው። ... "ነገር ግን ደነገጡና ፈሩ መንፈስም ያዩ መሰላቸው። እርሱም፦ ... እኔ ራሴ እንደ ሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት፥ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ አላቸው፡፡" (ሉቃ. 24፥37-39)

መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ። ... ሔዋን አጥንትና ሥጋ ነበራት ... ስለዚህ፥ ሔዋን ሥጋና አጥንት ከነበራት ወይም ስለነበራት መንፈስ አይደለችም። ... አዳም ሥጋና አጥንት አለውና እርሱም መንፈስ አይደለም። ሰው መንፈስ ነው የሚሉ ሰዎች የሚፎርሹት ገና ከመጀመሪያው፥ ከፍጥረትም ጅማሬ ነው ማለት ነው፡፡ ... እኛ ሥጋና አጥንት፥ ሥጋና ደም የሆንን ሰዎች ነን፤ ስለዚህ መናፍስት አይደለንም። ... ስለዚህ ሰው ምንድርን ነው? ሰው ሰው ነው። ሰው፥ ሰው ነው፡፡

መንፈስስ ምንድር ነው?

መንፈስ የሚለው ቃል በብሉይ ኪዳን ብዙ ተጠቅሷል። ... የሰውን መንፈስ ወይም በሰው ውስጥ ያለውን መንፈስም ያሳያል፡፡ ... ሰው መንፈስ እንዳለው እንጂ ሰው መንፈስ መሆኑን የሚናገር ትምህርት በብሉይ ኪዳን ውስጥ አይገኝም።

ብሉይ ኪዳን ስለ ሰው መንፈስ ይናገራል፤ ሲናገር ግን በሰው ውስጥ ስላለ መንፈስ እንጂ ሰው ራሱ መንፈሱ መሆኑን አይናገርም፡፡ ... ለምሳሌ፥ ምሳ. 20፥17 "የሰው መንፈስ የእግዚአብሔር መብራት ነው የሆዱን ጕርጆች ሁሉ የሚመረምር።" ሲል፥ መንፈስ ሰው መሆኑን ወይም ከሰው ጋር እኩል ነገር መሆኑን ሳይሆን በሰው ውስጥ የሚገኝ መሆኑን አመልካች ነው፡፡

ሌሎችም በርካታ ስፍራዎች ይህን ያሳያሉ፤ "መንፈስህ (ያንተ መንፈስ) በእኔ ላይ ሁለት እጥፍ ይሆን ዘንድ እለምንሃለሁ"፤ "የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ ዐርፎአል"፤ ... "የቂሮስን መንፈስ አስነሣ"፤ ... ሲል ኤልያስ፥ ቂሮስ፥ ... ሰዎቹ ናቸው፤ መንፈሱ የሰውየው ወይም በሰውየው ውስጥ ያለው ነው። ... ሰውየው ራሱ መንፈስ መሆኑን ሳይሆን መንፈሱ የሰውየው መሆኑን አመልካች ነው። ሰው መንፈስ መሆኑን ብሉይ ኪዳን አይናገርም፡።

... ዘካ. 12፥1 ... "ሰማያትን የዘረጋ፥ ምድርንም የመሠረተ፥ የሰውንም መንፈስ በውስጡ የሠራ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦" ይላል። የሰውንም መንፈስ በውስጡ የሠራ! ... በብሉይ ኪዳን አንዴም ሰው ሰው ብቻ እንጂ መንፈስ መሆኑ አልተጻፈም። የሰው መንፈሱ በውስጡ የሚገኝ የማንነቱ ክፍል ነው፡፡

በአዲስ ኪዳንም ሰው መንፈስ ነው ተብሎ አልተነገረም፡፡

ሮሜ. 1፥9 "በልጁ ወንጌል በመንፈሴ የማገለግለው እግዚአብሔር ምስክሬ ነውና፤" ይላል፤ 'በ' የሚለው አያያዥ የሚያሳየው ሰው እራሱ መንፈስ መሆኑን ሳይሆን መንፈስ በሰው ውስጥ ያለ መሆኑን ነው።

1ቆሮ. 2፥11 "በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው?..." ሰው መንፈስ ሳይሆን በሰው ውስጥ መንፈስ አለ ነው የሚለን።

1ተሰ. 5፥23 "የሰላምም አምላከ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ።" ጳውሎስ ... ይህ የሚያሳየን መንፈስ፥ ነፍስ እና ሥጋ፥ 'ሁለንተናችሁ' የተባለው የሰው ማንነት ውስጥ የተካተቱ ክፍሎች መሆናቸውን እንጂ ሰው መንፈስ መሆኑን ነፍስ ያለውና በሥጋ ውስጥ የሚያድር መሆኑን አያሳይም፡፡

የስሕተቱ ምንጭ

ታዲያ ይህ ሰው መንፈስ ነው የሚል ትምህርት ከየት መጣ? ለምንስ መጣ? ... በምዕራቡ ዓለም ይህ ስሕተት የቆየ ነው። ... በአገራችንም ዓመታት አስቆጠረ።

በምዕራቡ ዓለም በአንድ ከረጢት ውስጥ የታጨቁ በሽተኛ የሆኑ የከፉ ትምህርቶች አሉ፡፡ ከረጢቱ የቃል-እምነት፥ ወይም ቃለ እምነት ወይም Word of Faith ይባላል። ... 'ቃልህ አምነህ ካልከው፥ የፈለከውን ነገር መፍጠር ይችላል። ...' ይላሉ።

የቃለ እምነት ስሕተትን የብልጽግና ወንጌል ደግሞ ይሉታል። ... 'የሰብስቤነት ወንጀል' ብዬ ነው የምጠራው። ... 'የጤንነት ወንጌል' ደግሞ ይሉታል። ... ጤንነትም ወንጌልም የሌሉበት በሽታ ነው።

... ይህንን ችግረኛ፥ ... ትምህርት በአገራችን ... የዘሩት ጥቂት አይደሉም። "ዱሮ ሰው መንፈስ አይደለም፤ ሰው መንፈስ ነፍስና ሥጋ ነው ብዬ አስተምሬ ነበር። ... አሁን ሰው መንፈስ ነው፤ ነፍስ አለው፤ ሥጋ ውስጥ ያድራል ብዬአለሁ፡፡" ኃይሉ ዮሐንስ። "ሰው መንፈስ ነው፤ ነፍስ አለው፤ በሥጋ ውስጥ ነው ሚኖረው።" ዶ/ር ቶሎሳ ጉዲና።

... ኃይሉ በአንድ ወቅት እንደ መንፈሳዊ አባቱ እንደሚያየው የተናገረለት ኬነት ኮፕላንድ የዚህ አስተማሪ ነው። ስለዚህ የዚህ የኃይሉ ዮሐንስ፥ 'ሰው መንፈስ ነው' ትምህርት ምንጭ ኮፕላንድ ነው ማለት ነው። ኬኔት ኮፕላንድ ደግሞ ትምህርቶቹን የኮረጀው ከኦራል ሮበርትስ እና ኬኔት ሄግን ነው፡፡

... ሄግን ራሱ ትምህርቱን ያገኘው ከE. W. Kenyon ነው። ... "The spirit is the real man... Your body is not you. Your mind is not you... Your mind and body are merely the instruments of your spirit, the real YOU."

አዲሱ ሐዋርያዊ ዳግም ሥሪት (አሐዳስ ወይም NAR) በሚባለውን እንቅስቃሴ ውስጥ የተተበተቡት እኮ ፓስተር ቄስ ዶክተር ቶሎሳንም ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ አበሾችም ናቸው። ... 'አምስቱ ቢሮዎች' ብለው የሐዋርያትና ነቢያትን አገልግሎት የሚያደናንቁና የሚያራግቡት ... ናቸው።

የ'ሰው መንፈስ ነው' ትልልቅ አደጋዎች

አደጋ አንድ፤ መንፈስ ስለሆንን አንረክስም

የመጀመሪያው አደጋ፥ 'ሰው መንፈስ ከሆነ በሥጋው ከሚያደርገው ርኩስት መንፈሱ የታተመች ናትና አያገኛትም፤ አትረክስም።' የሚል ግንዛቤ ነው። ... ገና ከመጀመሪያው ምዕት ዓመት ጀምሮ የነበረ ግኖስቲሲዝም ... አካላዊውን ክፉ፥ ረቂቁንና የማይታየውን በጎ የማድረግ፥ ... ትምህርት ነበረ።

ሰው መንፈስ ነው የሚሉ ሰዎች አደገኛ ትምህርት መንፈስ ስለሆንን በሥጋ ለሚደረግ ኃጢአት ፈቃድ የመስጠት ዝንባሌ ነው፡፡ ... "በሥጋ የምናደርገው ኃጢአት ሥጋችንን ያረክሰዋል፤ ነፍሳችንን አይበክላትም፥ በተለይም መንፈሳችንን አይነካትም..." ወደሚል የድፍረት ኃጢአትም ይጋብዛቸዋል።

ይህ ግን ለቀቅ ማለት ሳይሆን ልቅ መሆን ነው፡፡ ... 2ጴጥ፣ 2፥18-19 ... "ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው፦ አርነት ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጡአቸዋል..." ... ኃጢአት ከቱታ ወደ ሰውነት ሳይሆን እንዲያውም ከሰውነት፥ ከውስጥ፥ ከልብ ወደ ቱታው የሚመጣ ነገር ነው። ማር. 7፥20-23 "... ይህ ክፉው ሁሉ ከውስጥ ይወጣል ሰውን ያረክሰዋል።" ይላል።

... 1ቆሮ. 6፥19-20 "... ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? ... ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።" ... እዚህ ሥጋችን ነው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ የተባለው፡፡

አደጋ ሁለት፤ እኛ አማልክት ነን

ሁለተኛው የ'ሰው መንፈስ ነው' ስሕተት ትልቅ አደጋ፥ ሰው አምላክ ነው ማሰኘቱ ነው። እንዴት ነው የሚያሰኘው? ቢባል፥ እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ ሰውም መንፈስ ነው፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ከሆነ፥ ሰውም መንፈስ ከሆነ፥ ሰው እግዚአብሔር ነው ማለት ነው። ... እኛ ትንንሽ እግዜሮች ነን፥ ትንንሽ አምላኮች ነን፥ አማልክት ነን የሚሉት ለዚህ ነው።

... ትንንሽም ይሁን ትልልቅ አማልክት ነን የሚሉት ከዚህ 'መንፈስ ነን' ከሚለው ትምህርት ጋር የተያያዘ ነው። ... 'እግዚአብሔር በቃሉ ከፈጠረ እኛም በቃላችን መፍጠር እንችላለን፤' የሚል ነው። ... እኛ የእግዚአብሔር 'ክላስ' ነን፤ የእግዚአብሔር kind ነን፤ ይላሉ፡፡ ... እግዚአብሔር ዓይነት አይደለም። ... እርሱን የሚመስል ሌላ የለም።

... ኃይሉ ዮሐንስም፥ 'አምላክ ምንድነው ሚወልደው? አማልክትን ነው።' ብሏል ...። መምሰልና መሆን የተለያዩ ናቸው። ... Little 'G' godም የትኛው 'G godም ማናችንም አይደለንም። ሰው ነህ፤ ሰው ነሽ፤ ሰው ነን።

... 'እኔና አብ አንድ ነን' ያለ ከኢየሱስ በቀር ሌላ የለም። ይህን ያለው ደግሞ የሆነው እርሱ ነው። ... እርሱና አብ አንድ ናቸዋ! ዛሬ ግን ሌሎች ተሳዳቢዎች በቅለውልናል። ... ኃይሉ ዮሐንስ እና ይህን መሰል ስድብ በእግዚአብሔር ላይ የምትናገሩ፥ ተሳድባችኋል፤ አንተና አብ አንድ አይደላችሁም። ... እናንተን ማየት አብን ማየት አይደለም።

... ጌታ፥ 'እኔና አብ አንድ ነን' ሲል፥ በአይሁድ ግምት ተሳድቧል። እርሱ ግን አምላክ ስለሆነ፥ እግዚአብሔር ስለሆነ፥ በሥጋ የመጣ ቃል ስለሆነ አልተሳደበም፡፡ ... 'ሰው መንፈስ ነው' ለሚለው ሙግት ከሚያቀርቧቸው ጥቅሶች አንደኛውን ምላሽ፥ “'እናንተ አማልክት ናችሁ' ይላልና አማልክቶች ነን።' ይላሉ፡፡ ... ቃሉ፥ 'አማልክት' ስላላቸው፥ አማልክት የተባሉ ሁሉ ትልልቅም ትንንሽም እግዚአብሔር ናቸው ማለት አይደለም።

መዝ. 82፥6 "እኔ ግን፦ አማልክት ናችሁ፥ ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ፤" ባለበት መዝሙር ውስጥ ... ይህ ክፍል ስለ አለቆች፥ ዳኞች፥ ፈራጆች መናገሩን የምናውቀው ከቀጣዮቹ ጥቅሶች ነው። ከ2-4 ... "እስከ መቼ ሐሰትን ትፈርዳላችሁ? ... ለድሆችና ለድሀ አደጎች ፍረዱ..." ... ደግሞም ቁጥር 7 ላይ፥ "ነገር ግን እንደ ሰው ትሞታላችሁ..." ይላል። መላእክት አይሞቱምና ይህ ስለ ሰው መናገሩ እንደሆነ ይታያል፡፡

... ጌታ በዮሐ. 10፥34-36 ... "እኔ፦ አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን? ... እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን፦ ትሳደባለህ ትሉታላችሁን?" ... ጌታ ይህንን ያለው ... እነዚያ ፈራጆች ብቻ የሆኑት ኤሎሂይም ከተባሉ፥ እኔ ልጅ ነኝ ስላልኩ ይህን እንዴት ትላላችሁ?' ነው። ... ስለ አማልክት ወይም ሰው አምላክ ነው ስለሚሰኝ ስሕተት አይናገርም።

ከመንፈስ መወለድ መናፍስት ያደርገናል?

... 'ሰው መንፈስ ነው' የሚሉ ሰዎች ይህን ሲሉ ሰው አምላክ ነው ማለታቸው ነው። ... 'ሰው መንፈስ ነው' የሚሉ ሰዎች፥ 'ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደ ደግሞ መንፈስ ነው። አይልም ወይ? ...' ይላሉ፡፡

... ዮሐ. 3፥6 ያንን ይላል? ማለት፥ ሰው መንፈስ መሆኑን ይናገራል? አይናገርም። ጌታ እዚያ የሚናገረው ስለ ዳግም ልደት ስለሆነ ዳግም በመወለድ የእግዚአብሔር ልጅ ስለመሆን ነው። ... ኒቆዲሞስ ... መወለድን የተረዳው በሥጋ እንደመወለድ ነው። ... ጌታ ለኒቆዲሞስ በሥጋ መወለዱና የአብርሃም ልጅ መሆኑ ሳይሆን፥ ዳግመኛ መወለዱ፥ ከውኃና ከመንፈስ መወለዱ ብቻ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግቢያው እንደሆነ ነው የነገረው። ከመንፈስ መወለድ ዳግመኛ መወለድ ነው።

... 'ከመንፈስ መወለድ' የሚባለው ሐረግ ... ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው ሲል መንፈሳዊ ማንነትን ያላብሰናል፤ የእግዚአብሔር ልጆች ያደርገናል፤ ... ዮሐ. 1፥11-13። ... ጌታን ስለተቀበልነው ልጆች ሆነናል፡፡ ልጆች ሆነናል ሲባል ከሰውነት ወደ መለኮትነት ተላልፈናል፤ ተሻግረናል ማለት አይደለም።

ከመንፈስ መወለድ ዳግም ልደት እና መንፈሳዊነት ነው

... ሮሜ 8፥14 "በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና፡፡" ... እኛ ልጆች የሆንን፥ የልጅነት መንፈስ ያለን ነን እንጂ መንፈሶች አይደለንም፡፡ እኛ እግዚአብሔርን አባ፥ አባት የምንጠራ ነን እንጂ የእግዚአብሔር ክላስ ወይም መደብ የሆንን እግዜሮች አይደለንም።

... ሮሜ 8፥9 "እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም።" ... አለ እንጂ "መንፈስ እንጂ ሥጋ አይደለችሁም" አላለም። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችን መንፈስ አያደርገንም፤ መንፈሳውያን ግን ያደርገናል፡፡

... 1ዮሐ. 3፥2 "ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፥ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን፡፡"

... ይህ አዲስ ሰው የሚባለው፥ ወይም አዲስ ፍጥረት የሚባለው በክርስቶስ ስንሆን የምንሆነው ማንነት ነው። 2ቆሮ. 5፥17 ... "ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።"

... መምሰል እንግዲህ ይህ ነው። ከመንፈስ መወለድም መንፈሳዊነት እንጂ መንፈስነት አለመሆኑን፥ ዳግም በመወለድ እንደ ልጆች መመላለስ፥ እንደ ሥጋ ፈቃድ ሳይሆን እንደ መንፈስ ፈቃድ መመላለስ መሆኑን ነው ያየነው።

መደምደሚያ፤ ሰው ሰው ነው፤ ዛሬም ነገም፥ ለዘላለምም፡፡

እኛ እግዚአብሔሮች ሳንሆን እግዚአብሔር በመልኩና በምሳሌው የሠራን ሰዎች እና ሰዎች ብቻ ነን። ፍጡራን ነን። ይህ ፍጡርነት ወይም ሰውነት ወይም ሰው መሆን፥ ልካችን ነው። ... ሰው መሆናቸው አናሳ ማንነት መሆኑን ሰይጣን ነበር ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በዔድን ገነት የነገራቸው። ዛሬም ሰው አይደለንም መናፍስት ነን፤ አማልክት ነን የሚሉን የማንን ጡሩምባ እየነፉልን መሆኑ ይግባን። የሰይጣን ማሚቶዎች እየሆኑ ነው።

በዔድን ገነት ሰይጣን ያለው፥ "እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ።" ነበር። ዘፍ. 3፥5። ... 'እንደ እግዚአብሔር እንድትሆኑ' በማለት ግን ከመምሰል ያለፈ ነውና የመምሰልን ወይም የመልክና ምሳሌን ሳይሆን የመሆንን ፍላጎት ተከለባቸው። ዛሬም፥ 'እንደ እግዚአብሔር ያለን፥ የእግዚአብሔር ክላስ' የሚሉት የማንን ግሳት እያገሱ እንደሆነ አንዘንጋ።

ሰውን በሥጋ ውስጥ ያድራል ሲሉ በሥጋ ውስጥ የሚያድር መንፈስ የሚያሰኙ ሰዎች መንፈስ ወደሆነው እግዚአብሔር በማስጠጋት መለኮትን ለማቀዳጀት መጣራቸው ነው። ሰው መለኮት አይደለም፤ ሰው ሰው ነው። ክቡር ሰው፡፡ ... ሰው እንደ መልክዓ እግዚአብሔርነቱ በዚህ አካል ሳለ ሰው ነው፤ ይህ አካሉ ፍጥረታዊ አካል ይባላል። በትንሣኤም አካል የሚሆነው፥ ከሙታን የሚነሣው አካል ሰው ነው። በትንሣኤም መንፈስ አይሆንም፤ አካል ይኖረዋል፤ ያ አካል መንፈሳዊ አካል ይባላል። ... "ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፥ መንፈሳዊ አካል ይነሣል።" 1ቆሮ. 15፥44።

... ራእ. 21፥3 ... "እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥" ይላል እንጂ "በመንፈሶች መካከል ያድራል" አይልም፡፡ ... አሁን ብቻ ሳይሆን ከትንሣኤ በኋላም ሰው መሆናችን ይቀጥላል እንጂ የእግዚአብሔር 'ክላስ' አሁን አይደለንም፤ ኋላም አንሆንም።

... ይህ ሰው መንፈስ ነው፤ ነፍስ ያለው በሥጋ ውስጥ የሚኖር የሚለው ትምህርት አዲስ ትምህርት አይደለም። ... 'ሰው መንፈስ ነው' የሚሉትና የሚያስብሉት፥ 'ሰው መንፈስ ስለሆነ፥ ሰው እግዚአብሔር ነው፤' ለማሰኘት ነው። ... ምንጩም ዔድን ገነት ነው፤ ጀማሬው ሔዋንን ያሳተው የቀደመው እባብ የተባለው ሰይጣን ነው። ይህ ትምህርት ገና ከመጀመሪያ ወላጆቻችን ጀምሮ የነበረ፥ ያረጀ፥ ግን ቡትቶውን አድሶ የመጣ አጋንንታዊ ትምህርት ነው።

2ቆሮ. 11፥3-4 "ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለከርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ፡፡ የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ፡፡"

ሌላ ኢየሱስ፥ ልዩ መንፈስ፥ ልዩ ወንጌል አለ። እንዲህ ያሉ ስሕተቶችን አንታገሥ።

ዋቢዎች

  • ግርማዊ፤ የብልጽግና ወንጌል፤ አዲስ አበባ፤ 2000 ዓ. ም. ።
  • ዘላለም መንግሥቱ፥ ሰው ምንድርነው? ... የቪድዮ ተከታታይ ትምህርት፤ 2020። (Youtube links)
  • ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፤ 1948 ዓ. ም.።
  • ደስታ ተክለ ወልድ፤ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት፤ 1962 ዓ. ም.።
  • ጳውሎስ ፈቃዱ፤ ደ'ሞ የእግዚአብሔር አቻ ሆንን!? መጣጥፍ።
  • ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ፤ ፕሮፌሰር የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ ፥ 2008 ዓ. ም.
  • Copeland, Spirit, Soul and Body I
  • Copeland, Following the Faith of Abraham I
  • Copeland, K. Our Covenant with God, 1976.
  • Exodus TV Show (Youtube link)
  • Guzik, David. David Guzik's Commentary...
  • Hoekema, Anthony A. Created in God's Image, 1986.
  • Hunt, Dave. Beyond Seduction, 1986.