ክሪስቶሎጂካል ሥነ-ምግባር
በክርስትና ሥነ-መለኮት ውስጥ፣ የክርስቲያን ሥነ-ምግባር ማለት የተጻፉ ደንቦችን፣ የሙሴን ሕግጋት ወይም ማኅበራዊ ወጎችን በደረቁ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን፣ "ኢሚታቲዮ ክሪስቲ"፣ ክርስቶስን መምሰል በሚለው ጥልቅ ጽንሰ-ሐሳብ ላይ ያተኩራል። የክርስቲያን ሥነ-ምግባር በመሠረቱ ስለ "ትክክልና ስህተት" ፍልስፍናዊ ትንታኔ ማወቅ ሳይሆን፣ ራሱ "መንገድ፣ እውነትና ሕይወት" ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ማወቅና እርሱን መከተል ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ረቂቅ የሆነው የእግዚአብሔር የቅድስና ፈቃድ በሥጋ ፣ሰው ሆኖ የተገለጠበት ፍጹም የሥነ ምግባር አብነት ነው። እርሱ ራሱ ሥነ ምግባር ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ የጽድቅ ፍጹም መገለጫና ለሰው ልጆች ሁሉ የማያወላውል አርአያ ነው። እርሱ በምድር ላይ በተመላለሰበት ዘመን ሁሉ፣ ኃጢአት የሌለበት (ዕብራውያን 4:15) ንጹሕና ምሳሌያዊ ሕይወት ኖሯል፤ ያጋጠሙትንም የሰውን ልጅ ፈተናዎች ሁሉ በአሸናፊነትና በጽናት ተቋቁሟል። አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት በምድረ በዳ በነበሩት ሦስት ታላላቅ ፈተናዎች (ማቴዎስ 4:1-11)፣ ኢየሱስ የሰው ልጅ ሊወድቅባቸው የሚችሉ ጥልቅ የሥነ ምግባር ፈተናዎችን ፊት ለፊት ተጋፍጧል፤ እነርሱም፡- የተሰጠውን መለኮታዊ ኃይል ለሥጋዊ ፣ለራስ ወዳድነት ፍላጎት ስለመጠቀም፣ የእግዚአብሔርን ጥበቃና ተስፋ ለታይታ ስለመፈተን፣ እና የዓለምን ሥልጣንና ክብር በአቋራጭ ለማግኘት ሲል ለሰይጣን ስለመገዛት ነበሩ ፈተናዎቹ። በእያንዳንዱ አስጨናቂ ጊዜ፣ የተጻፈውን ቃሉን በትክክል በመጥቀስ እና በአብ ዘላለማዊ ፈቃድ ላይ ሙሉ በሙሉ በመታመን ሳይወድቅ ጸንቶ ቆሟል።
ታላቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አጣብቂኝ፡ በዝሙት የተያዘችው ሴት (ዮሐንስ 8:1-11)
ፈሪሳውያንና ጻፎች አንዲት ሴት በዝሙት ስትሠራ ይዘው ወደ ኢየሱስ አምጥተው፣ ሊከሱት ፈልገው ከፍተኛ የሥነ-ምግባርና የሕግ አጣብቂኝ አዘጋጁለት፡ "ሙሴ በሕጉ እንደነዚህ ያሉት እንዲወገሩ አዟል፤ አንተስ ምን ትላለህ?" አሉት። ይህ ቀላል ጥያቄ አልነበረም፤ የሙሴን ሕግ መፈጸም ከተፈለገ ሴቲቱ በድንጋይ ተወግራ መገደል አለባት ፤ ነገር ግን ይህን ቢያዝ የሮማውያንን የሞት ቅጣት ሕግ መጣስ ይሆንበታል፣ የፍቅርና የምሕረት ስብከቱም ከንቱ ይሆናል፤ በሌላ በኩል ደግሞ እንድትለቀቅ ቢናገር የሙሴን ሕግ የሻረና ኃጢአትን የሚያበረታታ ሐሰተኛ ነቢይ ተብሎ በይፋ ይከሰሳል።
ኢየሱስ ግን የሰዎችን ግብዝነት በሚያጋልጥ ፍጹም መለኮታዊ ጥበብ አጣብቂኙን ሰበረው፡ "ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት"። በዚህ አስደናቂ ምላሹ የእግዚአብሔርን ፍትሕና የሕጉን ቅድስና አላጎደለም ፣ ኃጢአት መሆኑን አላስተባበለም፣ ነገር ግን ፈራጆቹ ራሳቸው ኃጢአተኞች መሆናቸውን በማሳየት ለሴቲቱ ጸጋን፣ ምሕረትንና አዲስ ሕይወትን ሰጣት። በመጨረሻም "እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ ከእንግዲህም ወዲህ ኃጢአት አትሥሪ" በማለት፣ ፍጹም እውነትንና ፣ኃጢአትን መጥላትን፤ ፍጹም ፍቅርን ፣ ኃጢአተኛን ማዳንን በአንድ ላይ ገለጸ።
በትምህርት አገልግሎቱም፣ ኢየሱስ የሙሴን ሕግ ውጫዊ ፊደል ብቻ ሳይሆን መንፈሱን በጥልቀት በመተርጎም፣ የሕጉን እውነተኛ መለኮታዊ ዐላማ ገልጧል። በታላቁ የተራራው ስብከት (ማቴዎስ 5–7)፣ ሥነ ምግባርን ከውጫዊ የሰዎች ዕይታና ድርጊት ወደ ውስጣዊ የልብ ዝንባሌ፣ አስተሳሰብና ሞቲቭ ያሸጋግረዋል፦ "... ለቀደሙት እንደ ተባለ ሰምታችኋል... እኔ ግን እላችኋለሁ..." (ማቴ 5:21-22, 27-28) በማለት ከግድያ ጀርባ ያለውን ቁጣን፣ ከዝሙት ጀርባ ያለውንም ምኞትን በማውገዝ የሥነ-ምግባርን መለኪያ ወደ ፍጹምነት ከፍ አደረገው።
ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው
ኢየሱስ 613 የነበሩትን የአይሁድ ሕግጋት በማጠቃለል፣ መለኮታዊ "አጋፔ" ፍቅር የሕግ ሁሉ ማሰሪያና ፍጻሜ መሆኑን አውጇል። በማቴዎስ 22:37-40 ላይ፣ ሁሉንም ትእዛዛት በሁለቱ ታላላቅ ትእዛዛት ሥር ያጠቃልላቸዋል፦ እግዚአብሔርን በፍጹም ልብ፣ ነፍስና አሳብ መውደድ፣ እና ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ። "በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕግም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል" በማለት አስተማረ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳብራራው (ሮሜ 13:10)፣ ግድያን ወይም ስርቆትን ስናስወግድ፣ ሕጉን በከፊል ፣ በአሉታዊ መልኩ እንፈጽማለን፤ ስንወድ ግን፣ ባልንጀራችንን ስለማንጎዳ ሕግን ሙሉ በሙሉ አሟልተን እንፈጽመዋለን።
ሕግን መፈጸም
በማቴዎስ 5:17-20 እንደተገለጸው፣ ኢየሱስ ሕግንና ነቢያትን ለመፈጸም እንጂ ለመሻር አሊያም ለማፍረስ አልመጣም። የሰው ልጆች በድካማቸው ምክንያት ሊጠብቁት ያልቻሉትን የእግዚአብሔርን ሕግ፣ እርሱ በፍጹም ታዛዥነቱና ኃጢአት በሌለበት ንጹሕ ሕይወቱ የእግዚአብሔርን የጽድቅ መስፈርቶች ሙሉ በሙሉ አሟልቷል። በእያንዳንዱ ፈተና ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆኖ በመቆም፣ እንዲሁም በመስቀል ላይ የሕጉን እርግማን ተሸክሞ በመሞት ሕግንና ነቢያትን አሳርፎ ፈጽሟል።
የክርስቲያን ሥነ ምግባር አንዱ ቁልፍና መሠረታዊ ገጽታ፣ መንፈስ ቅዱስ የሰው ልጆችን የሥነ ምግባር ስሜት በማደስ፣ በማንጻትና የተበላሸውን ሕሊናችንን በመምራት የሚጫወተው ማዕከላዊ ሚና ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ በአዳም ውድቀት ምክንያት የሰው ልጅ ጠቅላላ ተፈጥሮ ፣አእምሮ፣ ፈቃድ፣ እና ስሜት በኃጢአት እንደተበከለና፣ ያለ መለኮታዊ ፣ የመንፈስ ቅዱስ ጣልቃ ገብነት የእግዚአብሔርን ፍጹም ፈቃድ በራሱ ጥረት በትክክል መረዳትም ሆነ መፈጸም እንደማይችል ያስተምራል።
ሕሊና
በመካከለኛው ዘመን የነበረው ታላቅ የካቶሊክ ምሁር ቶማስ አኩይናስ የሰውን የሥነ-ምግባር ግንዛቤ በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፍለዋል፡ ሲንደሬሲስ (Synderesis) - ይህም ማለት የሰው ልጅ በተፈጥሮው የተሰጠው ክፉና በጎን ፣ትክክልና ስህተትን የመለየት አጠቃላይና ውስጣዊ እውቀት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኮንሴንቲያ (Conscientia) - ያንን አጠቃላይ እውቀት በተወሰኑ የሕይወት ውሳኔዎች ላይ በተግባር ማዋል ፣ ሕሊና ነው። አኩይናስ "የሰው ልጅ ሲንደሬሲስ ፣ መሠረታዊ የሞራል ዕውቀቱ በኃጢአት ውድቀት ምክንያት ሙሉ በሙሉ አልተበላሸም፤ አሁንም መልካሙን ይፈልጋል" ብሎ ያምን ነበር።
ነገር ግን በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሱት የፕሮቴስታንት ተሃድሶ ሥነ-መለኮት አባቶች ፣ እንደ ማርቲን ሉተር እና ጆን ካልቪን ይህንን የአኩይናስን ፍልስፍና አጥብቀው ተቃውመዋል። እነርሱ ጳውሎስን ጠቅሰው "ፍጹም ብልሹነት" በሚለው ትምህርታቸው መሠረት፣ በውድቀት ምክንያት የሰው ልጅ አካሉና ስሜቱ ብቻ ሳይሆን አእምሮውና ሕሊናውም ጭምር በኃጢአት ጨለማ እንደተበላሸ፣ እንደረከሰና እንደታወረ (ቲቶ 1:15) ያስተምራሉ። የሰው ሕሊና በተፈጥሮው ብቻውን ፣ በተወለደበት ሁኔታ አስተማማኝ የሥነ ምግባር መሪ ሊሆን ፈጽሞ አይችልም፤ ትክክለኛ መሪ ሊሆን የሚችለው በመንፈስ ቅዱስ ዳግም ሲወለድና በእግዚአብሔር ቃል ፣ ሲቀረጽና ብርሃን ሲበራለት ብቻ ነው ብለው አረጋገጡ።
ያልታደሰ አእምሮ፦ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ይህ ያልታደሰ ሥጋዊ አእምሮ ከእግዚአብሔር ቅዱስ ሕግ ጋር ያለውን ዘላለማዊ ግጭት በግልጽ ያሳያል። "የሥጋ አሳብ ለእግዚአብሔር ጥል ነውና... የእግዚአብሔርን ሕግ አይገዛምና... በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም።" (ሮሜ 8:7-8)። ስለዚህ የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ለውጥ የሚጀምረው ሕግን በማንበብ ሳይሆን፣ ከዚህ "የሥጋ አሳብ" ባርነት ነጻ በሚያወጣን፣ የድንጋዩን ልብ አውጥቶ የሥጋን ልብ በሚሰጠን፣ በመንፈስ ቅዱስ አዲስ የፍጥረት ሥራ (ዳግም ልደት - Regeneration) ነው።
በመንፈስ መመላለስ እና በአእምሮ መታደስ
ዳግም በመወለድ በአማኙ ውስጥ ማደሪያ ያደረገው መንፈስ ቅዱስ፣ የአማኙን ሕሊና በየዕለቱ እያጠራና እያስተካከለ ይመራዋል። ጌታ ኢየሱስ "እርሱ፥ የእውነት መንፈስ፥ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል" እንዳለ (ዮሐንስ 16:13)። ይህ መንፈስ ቅዱስ ወደ እውነት መምራት የሚከናወነው በዕለታዊ የአእምሮ መታደስ ሂደት ነው (ሮሜ 12:2)። ሕሊናችን አስተማማኝና ስህተት የሌለበት መሪ እንዲሆን ዘወትር በመንፈስ ቅዱስ ድምፅና በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መመዘን፣ መታነጽና መብራት አለበት። መንፈስ ቅዱስ ፍሬዎቹን በማፍራት ቅድስናን በውስጣችን ይሠራል። "በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ" (ገላትያ 5:16)።
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌ፡ ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ (1 ቆሮንቶስ 8)
በጥንቷ ቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትልቅ የሥነ-ምግባር አጣብቂኝና የሕሊና ክርክር ተፈጠረ። በመንፈሳዊ ዕውቀት የጎለመሱ አንዳንድ ክርስቲያኖች "በዓለም ላይ ጣዖት ከንቱ ነው፣ ለጣዖት የታረደውም ሥጋ ተራ ሥጋ ነው" ብለው እውቀታቸውን ተጠቅመው ለጣዖት የተሠዋውን ሥጋ በነጻነት ይበሉ ነበር። ነገር ግን ገና ከጣዖት አምልኮ የወጡ ሌሎች ፣ ደካማ ሕሊና ያላቸው አማኞች ይህንን ሲያዩ ይሰናከሉና ሕሊናቸው ይቆስል ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ እዚህ ላይ የክርስቲያን ነጻነት እና የላቀውን የፍቅርን ሕግ ያስተምራል። በመንፈስ ቅዱስ የዳበረና የታደሰ ሕሊና፣ መብትና እውቀት ስላለው ብቻ ራስ ወዳድ ሆኖ አያደርግም፤ ይልቁንም "እውቀት ያስታብያል፣ ፍቅር ግን ያንጻል። ይህ መብቴ ወንድሜን የሚያሰናክል ከሆነ፣ ወንድሜ እንዳይጠፋ ለዘላለም ሥጋ አልበላም" በማለት፣ የሌላውን ደህንነት ከግል ነጻነቱ ፣ መብቱ ያስበልጣል።
የክርስቲያን ነጻነት ፦ እውነተኛ የክርስቲያን ነጻነት ማለት ሕግን ጥሶ የፈለጉትን ኃጢአት የመሥራት አሊያም ሥጋዊ ምኞትን የማርካት ፈቃድ ሳይሆን፣ ከኃጢአት ባርነት አምልጦ በጸጋ ሥር የመኖር፣ እና እግዚአብሔርን በፈቃደኝነት የማገልገል ክቡር ነጻነት ነው። "ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ ተገዙ" (ገላትያ 5:13)። በመንፈስ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ የታደሰና የተማረከ ሕሊና፣ እግዚአብሔር የሚወደውን ይወዳል፣ የሚደሰትበትን ያደርጋል፤ እንዲሁም እርሱ የሚጠላውን ክፋት አጥብቆ ይጠላል።
በእነዚህ ሁሉ እጅግ ፈታኝ ጉዳዮች፣ ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተቀመጠው እሴታዊ ተዋረድ ይመራሉ፦ አጋፔ ፍቅር እና ለእግዚአብሔር የበላይ ትእዛዛት መታዘዝ ምንጊዜም ከፍተኛውን ደረጃ ይይዛሉ። በመንፈስ ቅዱስ የዳበረውና ቃሉን ያጠናው ሕሊናችን፣ መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ ዝም ባለባቸው ዘመናዊና ዝርዝር ጉዳዮች (እንደ ቴክኖሎጂና ሕክምና ሥነ-ምግባር) ክፍተቶችን በጥበብ እንድንሞላ ይረዳናል፤ ነገር ግን ውሳኔያችን ሁልጊዜ ከእግዚአብሔር ከተገለጠው የቅድስና ፈቃድ ጋር ፍጹም መጣጣም አለበት።